የፍርድ ቤት መረጃዎች

የሥልክ መረጃ
992

እንኳን ደህና መጡ

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መልዕክት

የህብረተሰቡን የፍትሕ ፍላጐት ማዕከል ባደረገ መንገድ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለዜጎች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ በቀላሉ ተደራሽ፣ ተጠያቂነት የሠፈነባቸውና ግልጽ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ሥር ነቀል የማሻሻያ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ዓመታት ባስቆጠረው በዚህ የማሻሻያ ሥራ ጊዜያት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት ሆነው የቆዩ ኋላ ቀር አሠራሮችና ልምዶችን በማስቀረት፣ የባለድርሻ አካላትን ገንቢ አስተያየቶችን በመቀበልና በግብዓትነት በመጠቀም በተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማግኘት ተችሏል፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ በመረጃ ረገድ የታየው ለውጥ ነው፡፡ መረጃ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በመገንዘብ የፍርድ ቤቶችን መረጃዎች በአግባቡ መያዝ፣ ማንቀሳቀስ፣ ለሚፈለገው ተግባር ማዋልና ለህብረተሰቡ አመቺ በሆነ መልኩ ማቀበል ይቻል ዘንድ በተለያዩ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም ጀምረናል፡፡ በዚህም ተአማኒነት ያለውና ትክክለኛ የሆነ መረጃ መያዝና በቀላሉም ለህብረተሰቡ ለማድረስ ተችሏል፡፡

ህብረተሰቡ መረጃን ከፍርድ ቤቶቻችን በተለያዩ መንገዶች ሊያገኝ የሚችል ሲሆን በድረ ገጽና በሰው አልባ የስልክ አገልግሎት መረጃን ለማስተላለፍ በተደረገ ጥረት ጥሩ ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት አገልግሎቶች ላለፉት 3 ዓመታት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሙከራ ላይ የቆዩ ሲሆን አሁን የማስፋፊያ ሥራዎች ተካሂደው ሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አገልግሎቶቹን እየሠጡ ነው፡፡ በዚህ ድረ ገጽ የተሟላ መረጃ ማግኘት የሚቻል በመሆኑ ህብረተሰቡ በአገልግሎቱ እንዲጠቀም እየጠየቅሁ ሊታረሙ የሚገባቸውንም ሆነ ሌሎች በማሻሻያ ሥራዎቹ ላይ ያሉ አስተያየቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በአክብሮት እገልጻለሁ፡፡

ተገኔ ጌታነህ
ፕሬዝደንት ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት