የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸው ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ
/ Categories: News

የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸው ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ

የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸው ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ

የተሻሻለው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች በቅርቡ መጽደቃቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለጀመሩት የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ይህን የገለጹት የፍርድ ቤቱ አመራሮችና ዳኞች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የ2013 የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ሲወያዩ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

የፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ነጻነትም ሆነ የዳኞች ነጻነት በአሁኑ ጊዜ የተረጋገጠ መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ፕሬዜዳንትዋ ይህም ዳኞች ሕግን ብቻ መሠረት አድርገው ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችላቸው መሆኑን በመጥቀስ ዳኞች ይህን ነጻነት ከሙያዊ ሥነምግባር (Integrity) ጋር አቀናጅተው ወደተግባር ሊተረጉሙት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ የዳኝነት አገልግሉት ነጻነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነትን ከማሳደግ፤ የዳኝነት ጥራት፣ የዳኝነት ግልጽነትና ቅልጥፍና ከማሻሻል እንዲሁም የዳኝነት ተደራሽነትን ከማሳደግ አንጻር የተከናወኑ ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የዳኝነት አገልግሎት ነጻነትን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር በየደረጃው በዳኝነት መርሆዎች ላይ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች መመቻቸታቸው፣ የበጀት ነጻነት የሚከበሩባቸው አሠራሮች መጀመራቸው እንዲሁም የጸደቁ የፍርድ ቤቱ አዋጆችን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች መሻሻላቸውና በመሻሻል ላይ መገኘታቸው እንደስኬት ተጠቅሷል፡፡

የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልም የአሠራር ሥርዓቶችና አደረጃጀቶች ተሻሽለው ለዳኝነትም ሆነ ለቅድመና ድህረ ዳኝነት ጥራት የሚያስፈልግ የሰው ኃይል ፍላጎትና የግብዓት አቅርቦቶች እንዲሟላ መደረጉ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ጨምሮ የባለሙያዎችን ዕውቀትና ክህሎት የሚያጎለብቱ የትምህርትና ሰልጠና መርሐግብሮች እንዲዘጋጁ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ በሥር ፍ/ቤት የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀመር መደረጉ፣ የተከማቹ ውዝፍ መዛግብት እንዲጠሩ ለማስቻል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ እንዲሁም ጽዱና ምቹ የሥራ አካባቢዎች እንዲዘጋጁ መደረጋቸው የአገልግሎት ጥራትን ከማሳካት አንጻር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሆኑት በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲሁም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የዘጠኝ ወር የመዛግብት አፈጻጸም በተጠቃለለ መልኩ ሲታይ በተጠቀሰው ጊዜ 118,417 መዛግብት ዕልባት እንዲያገኙ ዕቅድ ተይዞ 119,413 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 100.84 በመቶ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ለማሳደግ እንዲረዳ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አምስት ተጨማሪ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማዕከላትን በመክፈት በኢፋይሊንግ ከ9 ክልሎች የተላኩ 1,456 መዝገቦችን ለማስተናገድ የተቻለ ከመሆኑም በላይ በ1801 መዝገቦች 2,232 ባለጉዳዮችን በቪዲዮ ኮንፍረንስ ለማከራከር የተቻለ መሆኑም በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡

በዘጠኝ ወር ውስጥ ለፍ/ቤቶች ከቀረቡ መዛግብት አንጻር በሶስቱም ፍርድ ቤቶች ካለፈው ተሻግረው፣ አዲስና እንደገና ተከፍተው ከቀረቡ 162,615 መዛግብት መካከል 119,413 መዛግብት ዕልባት አግኝተው 43,202 በመሻገራቸው የፍርድ ቤቶችን የማጥራት አቅም 97.91%፣ የመጨናነቅ ሁኔታ 1.36 እና የክምችት ምጣኔ 0.36 ለማድረስ እንደተቻለም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የፍርድ አፈጻጸም ቅልጥፍናን ከማሳደግ አኳያም 35,471 መዛግብትን መመርመር እና 3,374 ፍርዶችን/ውሳኔዎችን ማጣራት እንደተቻለና 5,618 የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ከዕዳ ዕገዳ ነጻ መሆናቸውን አረጋገግጦ የሀራጅ ሽያጭ በማካሄድ ከተለያዩ ገቢዎች ብር 322,175,918.32 በማሰባሰብ ለፍርድ ባለመብትና ለመንግሥት ብር 453,109,694.59 ለመክፈል እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎቶች እና ዳኞች የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም በተናጠል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የበጀት ጥያቄ ላይ በምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ
Next Article የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ቁልፍ የትኩረት መስክ እንዲሆን አስተያየት ቀረበ
Print
230