የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ቁልፍ የትኩረት መስክ እንዲሆን አስተያየት ቀረበ
/ Categories: News

የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ቁልፍ የትኩረት መስክ እንዲሆን አስተያየት ቀረበ

በአማካሪ ድርጅት እየተዘጋጀ ያለው ሶስተኛው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች በቀረበበት መድረክ የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ከቁልፍ የውጤት መስክ መካከል አንዱ እንዲሆን አስተያየት ቀረበ፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅ ድርጅት እና ሂደቱን እንዲከታተል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ ረቂቅ ስትራቴጂካዊ ዕቅድንና የዝግጅት ሂደትን የተመለከተ ሪፖርት ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶችና ም/ፕሬዝደንቶች ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አቅርበው ተጨማሪ ግብአት ሰብስበዋል፡፡

አማካሪ ድርጅቱ ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት ካካሄዳቸው የትንተና ጥናቶች ውጤት በመነሳት የለያቸውን ቁልፍ የትኩረት መስኮችን አቅርቧል፡፡  1. የዳኝት ነጻነት፣ ገለልተኛነት እና ተጠያቂነት፤ 2. የዳኝት ቅልጥፍና፤ 3. የዳኝነት ጠራት፤ 4. የዳኝነት ተደራሽነት፤ 5. ውጤታማ ኮሚዩኒኬሽን፤ አጋርነት እና የገጽታ ግንባታ፤ እና 6. ተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታ የስትራቴጂካዊ ዘመኑ ቁልፍ የውጤት መስኮች ናቸው፡፡

በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ የኢኮቴ (የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ) ተጠቃሚነት ተደራሽነትን፤ ቅልጥፍናንና ጥራትን ውጤታማ ለማድረግ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ተደርጓል፡፡  ይሁን እንጂ የፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት ማሻሻያ ትኩረት አድርጎ ከሚንቀሳቀስባቸው መስኮች መካከል ወረቀት አልባ አገልግሎት ማስጀመር መሆኑን በአጽንኦት የገለጹት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ም/ፕሬዝደንት  ክበር አቶ ሰለሞን አረዳ የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ቁልፍ የትኩረት መስክ አንዲሆን ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጥ የዳኝት አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ የወረቀት ስራን ለመቀነስ እና የመዛግብት ቅብብሎሽን ዲጃታል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አዲሰ ተሸሽሎ የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 በአንቀጽ 50 ፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ዳኝነት የመስጠት ተልዕኳቸውን (Automated) በሆነ መንገድ እንዲያከናወኑ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ይንን መነሻ በማድረግም ምክትል ፕሬዝደንቱ የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ራሱን የቻለ የትኩረት መስክ አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡  

በግብአት ማሰባሰቢያ ውይይቱ የረቂቅ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ መነሻ የሆኑት አማራጭ ራዕይ፤ ተልዕኮ እና እሴቶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸው ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ
Next Article ለ68 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የዳኝነት ክፍያ አገልግሎት ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሔደ
Print
109