ለ68 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የዳኝነት ክፍያ አገልግሎት ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሔደ
/ Categories: News

ለ68 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የዳኝነት ክፍያ አገልግሎት ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሔደ

ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የቆየውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ እና የአከፋፈል ሥርዓት ለማሻሻል ተዘጋጅቶ በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግንቦት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል የግማሽ ቀን ውይይት ተካሔደ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመራሮች እንዲሁም ዳኞች፣ ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ምንም ማሻሻያ ሳይደረግበትና ትኩረት ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ የቆየው የዳኝነት ክፍያ የፍርድ ቤትን ተደራሽነት በማያጣብብ መልኩ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ከደረሰበት ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መስተጋብር አንጻር ዘግይቶም ቢሆን ለማሻሻል ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ክፍያ እና የአከፋፈል ሥርዓት ረቂቅ ደንብ አዘጋጅተው በመድረኩ ላይ ለውይይት ያቀረቡት ቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩትና አሁን ደግሞ ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ታፈሰ ይርጋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምሕርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር በላይ ትዕዛዙ ናቸው፡፡

ረቂቅ ደንቡ ስድስት ክፍሎች እና 26 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ረቂቅ ደንቡ የተዘጋጀበት ዓላማ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ የሆነ የዳኝነት ክፍያ እንዲያስከፍሎ ለማስቻል፣ የዳኝነት ክፍያን ፍርድ ቤቶች እንዲያስተዳድሩ በማድረግ ዘመናዊና ቀልጣፋ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱ ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የመንግሥት መ/ቤቶች የዳኝነት ክፍያ መክፈል አለባቸው ወይስ የለባቸውም፣ በሰበር ደረጃ የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች የዳኝነት ክፍያ ሊጠየቅባቸው ይገባል ወይስ መጀመሪያ ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚከፈለው የዳኝነት ክፍያ በቂ መሆን አለበት የሚሉና ሌሎች ተጓዳኝ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሰነዘሩ ጠቃሚ ሀሳቦችን በረቂቅ ደንቡ ውስጥ በማካተትና የመጨረሻ ቅርጽ በማስያዝ ረቂቅ ደንቡ ወደሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ የሚደረግ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በውይይቱ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሶስት ዓመት የተዘጋጀን የሥራ ዕቅድ መሠረት በማድረግ በሪፎርም ሥራ ላይ መሆናቸው ተገለጸ ሲሆን የሪፎርም ሥራውን ተቋማዊ ለማድረግ የፍርድ ቤቱን አወቃቀርና ሥልጣንን የሚመለከተው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እና የዳኞች አስተዳደር አዋጅ መጽደቃቸውን ተከትሎ የሪፎርም ሥራው እየሰፋና እየተጠናከረ በመሔድ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሪፎርም ሥራው ውስጥ እንደጥሩ ጅምር የሚታየው የፍርድ ቤቱ እንደተቋም ነጻ ሆኖ መስራቱ እንዲሁም ዳኞች የሚቀርብላቸውን የዳኝነት ጉዳይ በሕጉ መሠረት ብቻ በነጻነት እያዩ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የዳኝነት ነጻነት ከተጠያቂነት ጋር የተቆራኘ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን የሥራ ጥራትን ለማሻሻልና ተጠያቂነትንም ለማዳበር ሥልጠና ዋና መሳሪያ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ በተጓዳኝ የዳኞችን የሥነምግባር ደንብ እና የዳኞችን የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያ ለማጸደቅ ሥራው በሒደት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ጸድቆ ተግባራዊ ለማድረግ ፍርድ ቤቶች በዝግጅት ላይ መሆናቸው፣ መመሪያውን ሥራ ላይ ለማዋል ፍርድ ቤቶች እና ዳኞች ብቻቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉት የማይችሉ በመሆኑ ከጠበቆችና ከአቃቢያነ ሕግ ጋር ውይይት እንደሚደረግም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የኢኮቴ ተጠቃሚነትን ማሳደግ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ቁልፍ የትኩረት መስክ እንዲሆን አስተያየት ቀረበ
Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይላካል
Print
118