የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይላካል
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይላካል

የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 መጽደቁን ተከትሎ በፍርድ ቤቶች ከዳኞች ውጭ ያሉ የአስተዳር ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሔደ፡፡

 

በቤዝ ኢትዮጵያ ሆቴል ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ለግማሽ ቀን በተካሔደው ውይይት ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ለዚሁ ዓላማ በተቋቋመው ቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ደንብ 13 ክፍሎችና 105 አንቀጾች ያሉት ሲሆን በመድረኩ ላይ በኮሚቴው አባላት ቀርቦ በተሳታፊ ሰራተኞች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 

ረቂቅ ደንቡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሰው ሀብት ስራ አመራር ቦርድ አደረጃጀትን፣ የሥራ ምዘናን፣ የደመወዝ ስኬልና አበልን፤ የሰው ሀብት ዕቅድ፣ ስምሪት እና የሥራ አፈጻጸም ምዘናን፤ የሥራ ሰዓትና የፈቃድ ሁኔታን፤ የሠራተኞች ትምህርት እና ስልጠናን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን አካትቷል፡፡

 

በሌላ በኩል ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃ የሚስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ሁኔታን፤ የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነትን፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች የመረጃ አያያዝን፤ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን፣ ኃላፊነት እና የሰራተኞች መብትና ግዴታዎችን፤ የዲስፕሊን እርምጃዎች እና የቅሬታ አፈታትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም ረቂቅ ደንቡ ይዟል፡፡

 

በረቂቅ ደንቡ ይዘት ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በረቂቅ ደንቡ ዝግጅት በተሳተፉ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ረቂቅ ደንቡን ለማዳበር የሚረዱ አስተያየቶችን ደግሞ በግብአትነት እንደሚጠቀሙባቸው የኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

 

በረቂቅ ደንቡ ላይ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ከተደረገበትና ለፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚላክ ታውቋል፡፡

 

በቅርቡ በፀደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 39(2) ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች «ከዳኞች ውጭ ያሉ ሠራተኞች ምልመላ፣ ቅጥር፣ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ ሥልጠና፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የጥቅማ ጥቅም ክፍያ፣ የሰራተኞቸ የዲሲፒሊን እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚወሰነው አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣ ደንብ አማካኝነት ይሆናል» በሚል መደንገጉ የሚታወስ ነው፡፡

 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ለ68 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የዳኝነት ክፍያ አገልግሎት ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሔደ
Next Article በረቂቅ የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የአስተዳደር ሰራተኞች ግብአት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱ ሰራተኞች በፍርድ ቤቶች የማሻሻያ ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲሚያሰፋው ተገለጸ፡፡
Print
212