በፍትሃ ብሔር ፍርደ አፋጻጸም በሚታዩ ተግዳሮቶች እና ሊወሰዱ በሚገባቸው የማስትካከያ እርምጃዎች ላይ ምክክር ተደረገ
/ Categories: News

በፍትሃ ብሔር ፍርደ አፋጻጸም በሚታዩ ተግዳሮቶች እና ሊወሰዱ በሚገባቸው የማስትካከያ እርምጃዎች ላይ ምክክር ተደረገ

ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም/ ቢሸፍቱ/ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸውን ውሳኔዎችና ትእዛዞችን በማስፈጸም ሂደት በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና ሊወሰዱ በሚገቡ የማስትካከያ እርምጃዎች ላይ ከባልድርሻ እካላት ጋር ምክክር አደረገ።

 

በምክክር መድረኩ በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት የተዘጋጅ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል። በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ዳኛ እና በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ አይሸሱም መለሰ ለውይይት የቀረበው የዳሰሳ ጥናት የዳይሬክቶሬቱን የስራ ሂደትና አደረጃጀት፤ በፍርድ አፈጻጸም በዳይሬክቶሬቱ ውስጥ እና ከዳሬክቶሬቱ ውጪ የሚያጋጥሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶች፤ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቀነስ ሊውስዱ የሚገባቸው እርምጃዎች በዝርዝር ይዟል።

 

የተነሳሽነትና ቅንነት ማነስ፤ የፋይል አያያዝ ችግር፤ የተቋቋሙ ሲስትም አለመዘርጋት፤ የሰራተኛ አቅም ማነስ እና የሰራ ሰዓት አለማክበር በውስጣዊ ተግዳሮቶች ከተዘረዘሩት  መካከል ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በሃራጅ አዳራሽ አዘውትረው የማይጠፉ እና ግዢ የሚፈጽሙ ባለጉዳዮች (ደላሎች) በሌላ በኩል በተግዳሮትነት የተጠቀሱ ችግሮች ናቸው።

 

ከውጫዊ ተግዳሮቶች መካከል ለማስፈጸም የሚያስቸግሩ ውሳኔዎችና ትእዛዞች በፍርድ ቤቶች መሰጠት፤ ከመሬት አስትዳደርና ይዞታ ማረጋገጫ ተቋማት ትክክለኛ ፣ እውነተኛና የማያዳግም መረጃ አለመስጠት፤  መንገድ ትራንስፖርት ከተሽከርካሪ ጋር በተገናኘ እንደ እዳና እገዳ አለመኖር፣ ከቀረጥ ነጻ የገባና ቀረጥ የተከፈለበት መረጃዎችን ለይቶ አለማቅረብ፤ እና ከተሸከርካሪ ባለቤትነት ስም ዝውውር ጋር ተያይዞ ምልልስ መብዛት ዐብይ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ተገልጿል። 

 

በተመሳሳይ በፖሊስ በኩል ሁከት ለማስወገድና ፍርድ ለማስፈጸም የቁርጠኝነት ውስነት መኖር እና በተገኙበት እንዲያዙ ውሳኔ ያረፈባቸው ተሽከርካሪዎች እርምጃ መዘግየት ተለይተው የተጠቀሱ ተግዳሮቶች ሲሆኑ የወረዳና የክፍለ ከተማ ግንባታ ፈቃድ ሰጪ ቢሮዎች የሚሰጧቸው ግልጽነት የጎደላቸው መረጃዎች፤ የፍርድ ባለእዳ እና ባለመብት የግል ፍላጎቶች ውጫዊ ለፍርድ አፈጻጸም ሂደት መጓተት እንዲሁም አለመፋጸም አንኳር ምክንያቶች ናቸው በማለት የተገለጹ ናቸው።

 

በመጨረሻም የዳሰሳ ጥናቱ ለተግዳሮቶቹ ተነጻጻሪ የማስተካከያ እርምጃዎችና ምክረ ሃሳቦችን ጠቁሟል።

 

የምክክር መድረኩን መልዕክት በማስተላለፍ የተከፈቱት የፌ/ከ/ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪ ፍርድ በውዴታ ሳይሆን በግድ የሚፈጸም በመሆኑ ስራውን ክባድ ያደርገዋል ስለሆነም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀና ትብብር እና ሃላፊነትን በትጋት የመወጣት ቁርጠኝነት ያሰፈልጋል ብለዋል።

 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ዳኛ የሆኑት አቶ ተሾመ ሽፈራው በፍርድ አፈጻጸም ሂደት የባለድርሻ ሚና በሚል ርእስ ገለጻ አቅርበዋል። የምክክር መድረኩን የጋራ ውይይትም መርተዋል።

 

በምክክር መድረኩ የሶስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም ችሎት ዳኞች፤ የፍርድ አፋጻጸም ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች፤ የመሬት አስተዳደር እና የክፍለ ከተማ የግንባታ ፈቃድና መረጃ ቢሮዎች፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ትራፊክ ጽ/ቤት እና ሌሎችም ተሳትፈዋል ።

 

ፌ/ጠ/ፍ/ቤ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በረቂቅ የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የአስተዳደር ሰራተኞች ግብአት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱ ሰራተኞች በፍርድ ቤቶች የማሻሻያ ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲሚያሰፋው ተገለጸ፡፡
Next Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ዕለት በከፊል ክፍት ሆነው ይውላሉ፣
Print
99