በፍ/ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ
/ Categories: News

በፍ/ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን እና ተቋማዊ ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች ለማሻሻያ ስራው መሰረት የጣሉ እና ውጤታማ እንደነበሩ ተገለጸ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ በዳኞች አስተዳደር እና በሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተከናወኑ ተግባራትን እና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ክብርት ፕሬዚዳንትዋ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ባለፉት ወራት ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረታዊ ከሆኑት እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኞችን እና ተቋማዊ ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ሁለት መሠረታዊ አዋጆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቃቸውን ገልጸው እነዚህም የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

እነዚህን አዋጆች ተግባራዊ ለማድረግም በርካታ ደንቦችና መመሪያዎች እየጸደቁ እንደሚገኙ አመልክተው ከእነዚህ መካከል የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ፣ የዳኞች ሥነምግባር ደንብ እና የስራ አፈጻጸም መመዘኛ መመሪያ እንዲሁም የድጋፍ ሰራተኞች የአስተዳደር ደንብ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝም በመጪው በጀት ዓመት የዳኝነት ነጻነት ዋስትና በሆነው ተጠያቂነት ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው ለዚህም የህዝቡ እና የህግ ባለሙያው ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት የነበረውን በፍርድ ቤቶች የመዝገብ አፈጻጸም ሲገልጹም በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለ166,758 (አንድ መቶ ስድሳ ስድስት ሺሀ ሰባት መቶ ሃምሳ ስምንት) መዛግብት እልባት ለመስጠት ዕቀድ ተይዞ ለ171,276 (አንድ መቶ ሰባ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ስድስት) መዛግብት እልባት መሰጠቱንና ይህም የፍ/ቤቶችን የመዝገብ አፈጻጸም 102.7 በመቶ አድርሶታል ብለዋል፡፡

አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በ37,800 (ሰላሳ ሰባት ሺህ ስምንት መቶ) መዛግብት ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

እልባት ካገኙ መዛግብት መካከል 150,283 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሶስት) መዛግብት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኙ ሲሆን ይህም 87.74 በመቶ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ለፍርድ ቤቶች ከቀረቡ ልዩ ባህሪ ካላቸው ጉዳዮች ውስጥ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቶች እንዲመለከቱ በምርጫ አዋጁ ተልዕኮ በተሰጣቸው መሠረት ከስድስተኛው ሃገራዊ የምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ የምርጫ ሂደቱ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 21፤ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 24 እና በጠቅላይ ፍ/ቤት 29 በአጠቃላይ 74 ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ቀርበው በነጻነትና በገለልተኝነት የዳኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከነዚህ መካከል 57 በቅድመ ምርጫ፤ 4 በምርጫ ዕለት እና ቀሪዎቹ 13 ጉዳዮች በድህረ ምርጫ የቀረቡ ሲሆኑ የጉዳዮች ዓይነት ሲታይ ደግሞ 22 የወንጀል ጉዳዮች ሲሆኑ 52ቱ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነትን ግልጽነት ከማረጋገጥ አኳያ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን በመጥቀስም በዚህ መሠረት በሁሉም ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የማስቻያ ቦታ እጥረቶችን ለማቃለል ችሎቶች በፈረቃ መጠቀም የሚችሉበት መርሃ ግብር በማውጣት፤ ተጨማሪ የችሎት አዳራሾችና እስቴጆችን በማደራጀትና በየምድብ ችሎቶቹ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በማደራጀት የዳኝነት አገልግሎት በግልጽ ችሎት እንዲሰጥ እና ተገልጋዮች በግልጽ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከችሎት ውጪ እንያገኙ ማድረግ እንደተቻለ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኙ 5 ችሎቶች የICT ውጤት የሆኑ ዲጂታል የደምጽና የምስል መቅጫ መሳሪያዎች ከማይክ፤ ካሜራ እና ስክሪን ጋር እንዲገጠምላቸው በማድረግ ባለጉዳዮች በችሎት ውስጥና ውጪ የችሎት ሂደቱን እንዲከታተሉ በማድረግ የዳኝነት ግልጽነትን ማጠናከር እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

የዳኝነት ተደራሽነትን ለማስፋትም በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተወሰኑ ምድብ ችሎቶች አዲስ የቢሮ አደረጃጀት በመፍጠር በሌሎች ደግሞ ተጨማሪ ቢሮ በማዘጋጀት የዳኝነት አገልግሎቱን በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ እንደተቻለ ተጠቅሷል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮችን እንዳይመለከቱ ውክልና በተነሳባቸው ክልሎች ተዘዋዋሪ ችሎቶችን ቁጥር ከሁለት ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ በ15 ዳኞች የዳኝነት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የዳኝነት አገልግሎትን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በበጀት ዓመቱ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ክብርት ፕሬዚደንትዋ፣ ከዚህ አኳያ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚሰሩ 46 የርቀት ችሎት ማዕከላትን በክልል ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች በማስፋፋት በ2284 መዛግብት ለተከሰሱ 3,751 (ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ አንድ) ባለጉዳዮች ጉዳዮቻቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲከታተሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የዳኝነት አገልግሎቱን ተገልጋዮች ወዳሉበት ቦታ ተደራሽ ለማድረግ የተቻለ በመሆኑም ባለጉዳዮች አዲስ አበባ ቢመጡ ሊያወጡ ይችሉ የነበረውን ብር 6,620,000 (ስድስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃያ ሺህ) ለማዳን ተችሏል - እንደ መግለጫቸው፡፡

በተመሳሳይም በዘጠኝ ክልሎች የኢ-ፋይሊንግ ማዕከላትን በመክፈት 1,737 (አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ሰባት) የይግባኝና የሰበር መዛግብትን በማስተናገድ ከ 5,000,000 (አምስት ሚሊዮን) ብር በላይ ማዳን የተቻለ በመሆኑ ሲሆን በአጠቃላይ ተገልጋዮች አዲስ አበባ በመምጣት ሊደርስባቸው የሚችለውን ድካም፣ እንግልትና ጊዜ ከመቀነስ ባሻገር ሊያወጡት የሚችሉትን ብር 11,620,000 (አስራ አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ሃያ ብር) ማዳን ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ በሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የነበረውን በጀት አጠቃቀም ሲገልጹ በመደበኛ በጀት ከተፈቀደው የተስተካከለ በጀት ብር 680,498,257 (ስድስት መቶ ሰማኒያ ሚሊዮን አራት መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር) ውስጥ ብር 651,562,071.72 (ስድስት መቶ ሃምሳ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ ሰባ አንድ ብር) መጠቀም በመቻሉ አፈጻጸሙ 96 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ክብርት ፕሬዚደንትዋ በዚህ መግለጫቸው በበጀት ዓመቱ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እና በሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ጽ/ቤት የተከናወኑ ተግባራትን እንዲሁም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የወደፊት አቅጣጫዎች ዳስሰዋል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ዜና መግለጫ:- ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ስለመሆናቸው
Next Article በፍርድ ቤቱ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው
Print
111