የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ዓለም አቀፋዊ የዳኝነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ
/ Categories: News

የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ዓለም አቀፋዊ የዳኝነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ዓለም አቀፋዊ የዳኝነት መርሆዎችን እንዲሁም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥትን እና ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ረቂቅ ደንቡ ሲዘጋጅ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ዓለም አቀፍ የሕግ አማካሪ የሆኑት አሜሪካዊው ሚስተር ማይክል ከኒፍ ገለጹ፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሪፎርም አካል በሆነውና ማሻሻያ ተደርጎበት በቅርቡ በዳኝነት አስተዳደር ጉባኤ በጸደቀው የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ላይ ለፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከነሐሴ 15-25 ቀን 2013 ዓ.ም በአምስት ዙሮች በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከነሐሴ 15-16 ቀን 2013 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ደግሞ ለሁለት ቀናት የሚሰጠውን ሥልጠና ከነሐሴ 17-25 ቀን 2013 ዓ.ም በአራት ዙር እንደሚወስዱ ታውቋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ለተሳተፉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አሠልጣኙ ባደረጉት ንግግር የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ሐቀኝነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የዳኝነት መርሆዎች መሆናቸውን አስረድተው እነዚህ መርሆዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት የተካተቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለውይይት በቀረበው የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ መሠረት ዳኞች የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ ሆነው እንዲሁም ከቀረበላቸው ጉዳይ ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭት ያለመኖሩን በማረጋገጥ ሥራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዳኞች በጉዳዮች ላይ በሚሰጡት ውሳኔና ዳኝነት ግልጽነታቸውን (transparency) ለተገልጋዮች እንዲያሳዩ የሚጠበቅ ሲሆን የዚህም ተግባራዊነት ለፍርድ ቤቶች፣ ለዳኞች እና ለተገልጋዩ የሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንቡ ስለተዘጋጀበት ዓላማ እና አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ ካላቸው ራሳቸውን ለሙያዊ ሥነምግባር ግድፈት ሳያጋልጡ ሥራቸውን በሚፈለገው ብቃት ለማከናወን እንደሚረዳቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ደንቡ የሥነምግባር መርሆዎችንና የዳኝነት ተነጻጻሪ ግዴታዎችን፣ ለዳኝነት ሥራ የችሎታ ማነስ፣ ውጤታማ አለመሆንና የሥነምግባር ጥሰት፣ የሥነምግባር ደንብ ጥሰት ክስ ጉዳዮች የሚታዩበትን ሥነሥርዓት እና ሌሎችንም ድንጋጌዎች በውስጡ ያካተተ ነው፡፡

የደንቡ ሥራ ላይ መዋል በአንድ በኩል ዳኞች ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው በነጻነት ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትና ውሳኔያቸውም ከአድሎአዊነት የፀዳ፣ ገለልተኛነቱ የተረጋገጠ እና በሕግ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን በሌላ በኩል በደንቡ ላይ በተደነገጉ የሥነምግባር ግድፈቶች ምክንያት ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ ታውቋል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሐቀኛ፣ ብቃት ያላቸውና ውጤታማ በመሆን የሕዝቡን አመኔታ ያተረፉ እና በጽኑ መሠረት ላይ የተገነቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ቀጣይነት ያለው የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ደንቡ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመልክቷል፡፡

የደንቡ ሥራ ላይ መዋል በአንድ በኩል በሥነምግባር ደንብ ጥሰት የሚከሰሱ ዳኞች በሕግ አግባብ መዳኘታቸውን የሚያረገግጥ ሲሆን በሌላ በኩል ዳኞች የዳኝነት ሥራ የሚጠይቀውን ከፍተኛ የሙያ ብቃት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመጠበቅ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ዘንድ የሚኖራቸውን አመኔታ ለመጨመር፣ ተገልጋዮችም በሕገመንግሥቱ የተረጋገጡላቸውን መብቶች ከአድልኦ በጸዳና በፍትሐዊነት እንዲያገኙ ዋስትና የሚሰጥና ይህንም የሚያጠናክር ስለመሆኑ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ለአስር ቀናት የሚቆው የዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የፍትሕ ፕሮጀክት ትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፍርድ ቤቱ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው
Next Article በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ላይ ለዳኝነት ዘርፉ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ
Print
99