Welcome to Child Justice Project Directorate


ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሪጅስትራሮች ሲሰጥ የነበረዉ የተግባር ስልጠና ተጠናቀቀ
Selam Warga
/ Categories: News

ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሪጅስትራሮች ሲሰጥ የነበረዉ የተግባር ስልጠና ተጠናቀቀ

በፌዴራል ህግና ፍትህ ጥናት ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሪጅስትራሮች ከታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 4 ሳምንታት በተግባር ሲሰጥ የነበረዉ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል፡፡

ስልጠናዉ መድረክ ስለሬጅስትራሮች ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች ፣ህጎችን ከማስከበር አንፃር ያላቸዉ ሚና ፣በፍርድ አገልግሎት የዉክልና ስልጣን ህጉና በተግባር ያሉ ክፍተቶች ፣አዲሱ የዳኝነት ክፍያ ደንብ የዳኝነት አከፋፈል ስርዓት፣ በሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እንዲሁም በአሰራር የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸዉ ዙሪያ ገለፃና ማብራሪያ በተጨማሪ ተሳታፊዎች ባላቸዉ የስራ ሂደት በተግባር የሚገጥሟቸዉን ጉዳዮች በማንሳትና ከህጉ አንፃር ያለዉን አሰራር በማጣቀስ ሰፊ ዉይይት ተደርጓል፡፡

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና ሃሳብ አስተያየቶች ስልጠናዉን በሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሪጅስትራር ወ/ሮ ዙፋን ወ/ገብርኤል ፣የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ህይወት ማሙሸት እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናዉ ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ይህ ስልጠና በስራ ሂደት ዉስጥ የሚያጋጥሙ ጉድለቶችን እና የአሰራር ልዩነቶችን ህግን በተከተለ መንገድ ወጥ በማድረግ የመስራት ክህሎትን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደመሆኑ ስልጠናዉ በጉዳዩ የዳበረ ልምድና እውቀት ባላቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዋና ሬጅስትራሮች መሰጠቱ በጉዳዮቹ ላይ የበለጠ ተወያይቶ የጋራ ለማድረግ ሚናዉ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም ሪጅስትራሮች በፍርድ ቤቶች ውስጥ ካላቸው ሚና አንጻር መሰል ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጠቆም ሁሉም ሰልጣኞች ተቋማቱ የሚፈልጉትን ስነ-ምግባር ተላብሰዉና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን በማሳደግ በተመደቡበት የስራ ዘርፍ በቅንነትና በታማኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

Print
104