Welcome to Child Justice Project Directorate


በረቂቅ የህፃናት ፍትህ የስልጠና ሞጁል ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ ዉይይት  ተደረገ
Selam Warga
/ Categories: News, CJPO NEWS

በረቂቅ የህፃናት ፍትህ የስልጠና ሞጁል ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ ዉይይት ተደረገ

ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከዩኒሴፍ (UNICEF) ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉን የህፃናት ፍትህ የስልጠና ሞጁል ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ዉይይት መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም አድርጓል፡፡

በዉይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በፍትህ ስርዓቱ ዉስጥ ለሚያልፉ ህፃናት ህጉ ባስቀመጠዉ መሰረት የህፃናትን ፍትህ እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እና የህፃናቱን ጥቅምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ሁሉን አቀፍ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ረቂቅ ሰነዱን በማዳበር ረገድ ዳኞችና ሌሎች ተሳታፊ አካላት ድርሻቸዉ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የስልጠና ሞጁሉ የተዘጋጀዉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህራን ደ/ር እመቤት ሙሉጌታ እና ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ እንዲሁም በአዲስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና የቀድሞ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንትና በአሁኑ ሰዓት የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ደሳ ቡልቻ ሲሆን ሰነዱ የህፃናት ተስማሚ ፍትህ ትርጓሜና መርሆዎች፣የህፃናት እድገት፣ ከህፃናት ጋር መግባባት፣አለም አቀፍ ድንጋጌ፣በፍትህ ስርዓቱ ዉስጥ የሚያልፉ ህፃናት የህግ ማእቀፎችና ምሰሶዎች፣በወንጀል ጉዳይ ገብተዉ ለተገኙ ህፃናት ተስማሚ ፍትህ፣ ጎጂ ድርጊቶች፣ ጥቃትን የተቋቋሙ ህፃናት ጉዳይ፣ የድኅረ ገፅ የህፃናት ወሲባዊ ብዝበዛ ጥቃት ወንጀሎችና በወንጀል ጉዳይ ገብተዉ የተገኙ ህፃናት በኢትዮጵያ የሚሉ ይዘቶችን ያካተተ ነው።

በይዘቶቹ ላይ አዘጋጆች የሰጡትን ማብራሪያ መሰረት በማድረግ ለሰነዱ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ተነስተዉ ተገቢዉ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸው ተጨማሪ ግብዓቶችም ተወስደዋል፡፡

በመጨረሻም ዉይይቱን የመሩት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ ተክለሃይማኖት ዳኜ የስልጠና ሞጁሉን በተሰጡ ግብዓቶች በማዳበር የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ሌሎች የፍርድ ቤት አካላትን እንዲያሰለጥኑ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዉ Rapid Assessment on the Status and Capacity of the Child Friendly Justice System in the Conflict Affected Regions of Afar,Amhara and Tigray የሚል ከSave The Children ጋር የተሰራ የጥናት ውጤት አቅርበዋል፡፡

Previous Article ወንጀል ነክ ነገር ዉስጥ ገብተዉ የተገኙ ወጣቶችና በሴቶችና ህጻናት ችሎት ያጋጠሙ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች (Children in conflict with the law) በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ከፌደራልና ክልል ፍርድ ቤቶች ከተዉጣጡ ዳኞችና ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
Next Article በህጻናት ዝቅተኛ የወንጀል ተጠያቂነት እድሜ ላይ ያተኮረ ስልጠና እና ውይይት ከኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ተካሄደ
Print
818