Temesgen Alemayehu / Friday, June 30, 2023 / Categories: CJPO NEWS በቤተሰብ አስማሚነት ላይ የተዘጋጀ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሔደ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በተለይም በቤተሰብ አስማሚነት (Family mediation) ላይ ለፌደራል ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች እና ለሶሻል ወርክ ባለሙያዎች ያዘጋጀው የሥልጠና እና የውይይት መድረክ በኢንተር ኮንቲኔታል ሌግዢሪ ሆቴል ተካሄዷል፡፡ የሥልጠና እና የውይይት መድረኩ ዓላማ ህጻናት በሁለቱም ወላጆች የሚያድጉበትን ሁኔታ በማመቻቸት፤ ህይወታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ማድረግ ካልሆነም በወላጆች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት በመፍጠር ወላጆች በተስማሙበት ጉዳይ ተገዢ በመሆን ተስማምተው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበትን ዕድል ለማመቻቸት አስማሚዎች ባላቸው ሚና ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ፡፡ ስልጠናውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ ትምሕርት ክፍል መምሕር የሆኑት ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ሲሆኑ ስልጠናው የቤተሰብ አስማሚነት ወይም ሽምግልና የቤተሰብ መለየየት ወይም መፍረስ በሚከሰትበት ወቅት ወላጆች ወደ ፍርድ ሂደት ከመሔዳቸው በፊት ተስማምተው መፍትሄ በሚያገኙባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የቤተሰብ አስማሚነት ቤተሰብን ሁሉ የሚያካትት ሰፊ የሆነ ጽንሰ-ሐሳብ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር እመቤት ነገር ግን የፍቺ አስማሚነት (Divorce mediation) ከቤተሰብ አስማሚነት (Family mediation) ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ ቢመስልም ያላቸውን ልዩነት በመግለጽ የፍቺ አስማሚነት(Divorce mediation) የሚፋቱ ሰዎች ሲኖሩ የሚከናወን መሆኑንና አብዛኛውን ጊዜ ቀለብን፣ የንብረት ክፍፍልን እንዲሁም ሌሎች መሰል ጉዳዮችን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የቤተሰብ አስማሚነት (Family mediation) በስምምነት የሚኖሩ በጋብቻ ላይ ያሉ ሰዎችን እና ጋብቻ የሌላቸውን ጭምር የሚያካትት ሆኖ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግና መንከባከብ እንደሚገባቸው እንዲሁም የጋራ ንብረትን እንዴት በስምምነት ማስተዳደር እንደሚኖርባቸው መፍትሔ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር እመቤት አክለውም የአስማሚነት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ገልጸው አስማሚነት ሰዎች ግጭትን ለመፍታት የሚሰሩበት የሶስተኛ ወገን የግጭት አፈታት ዘዴ መሆኑንና ይህን ዘዴ በመጠቀም በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ግጭቱን ለመፍታት እንዲያስችላቸው በመሀከላቸው ያለው ግንኙነት መልካም እንዲሆን ማመቻቸትና መፍትሄዎች ከግለሰቦቹ የሚመነጭበትን ዕድል መፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በሥልጠናና በውይይት መድረኩ ላይ ሰፊ የሆነ ተሰትፎ የተደረገበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች ብቃትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡ ስልጠናው የተሰጠው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና በሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) ትብብር መሆኑ ታውቋል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article ተወላጅነትን በማረጋገጥ እና በመካድ ክርክር እንዲሁም በዘረመል ምርመራ አጠቃቀም ላይ የተዘጋጀ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሔደ Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የህጻናት ማቆያ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ Print 2003