Temesgen Alemayehu / Friday, June 16, 2023 / Categories: News, CJPO NEWS በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት የተደራጀው የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከል ተመርቆ ተከፈተ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ስር የተደራጀው የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ከሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት ያደራጀው የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከል ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ተመርቆ ተከፈተ፡፡ ማዕከሉ ጥቃት ደርሶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤቱ የሚታይ ሕጻናት በመደበኛው ችሎት ሳይቀርቡ ለሕጻናት ምቹ እንዲሆን ታስቦ የተደራጀና ከዳኞች ጋር በድምጽ እና በምስል ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው፡፡ ዳኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለተጠረጠሩነና በምስክርነት ለሚመጡ ሕጻናት የሚያቀርቡት የምስክርነት ጥያቄ በቀጥታ ሳይሆን ከሕጻኑ/ኗ ጋር በማዕከሉ ውስጥ ሆና ድጋፍ ለምታደርግ የማሕበራዊ ሳይንስ ባለሙያ (Social Worker) እየቀረበና ባለሙያዋ ጥያቄውን ለሕጻናቱ ተስማሚ በሆነ አኳኋን እየገለጸች የሚሰጠውን የምስክር ቃል ችሎቱ የሚሰማበት ሲሆን የፍትሕ አሠጣጥ ሒደቱንም ምቹ የሚያደርግ ነው፡፡ የፍትሕ ሒደቱ በማዕከሉ ድጋፍ እንዲታይ መደረጉ ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚጠረጠሩ ሕጻናት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲሰጡ እንዳይሸማቀቁ በማድረግ፣ በሕጻናቱ ላይ ሊከሰት የሚችለውን የስነልቦና መረበሽ በመቀነስና ቤታቸው ያሉ ያህል እንዲሰማቸው በማድረግ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ስለሚያስችላቸው ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ የሚረዳ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በማዕከሉ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና የሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የተጋበዙ የሥራ ኃላፊዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከማዕከሉ ምረቃ በፊት ተጋባዥ እንግዶቹ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአዲስ ከተማ ምድብ ችሎት ከሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተመሳሳይ ሁኔታ ተደራጅቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠኝ ምድብ ችሎቶች የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ በሥነሥርዓቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ሕብረተሰቡ በሕጻናት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲያደርግ የሚያበረታታ ስለመሆኑም በሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ በክልል ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎቱን ለሕጻናት ተደራሽ ለማድረግ በሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በኩል እየተደረጉ ስለሚገኙ ጥረቶችም በሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ በዳኛ ተክለሐይማኖት ዳኜ ለጎብኝዎቹ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት Previous Article ፍ/ቤቶች የሕጻናትን መብቶችና ጥቅሞች ከማስከበር አንጻር ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኝ ተጠቆመ Next Article ተወላጅነትን በማረጋገጥ እና በመካድ ክርክር እንዲሁም በዘረመል ምርመራ አጠቃቀም ላይ የተዘጋጀ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሔደ Print 2185