Welcome to Child Justice Project Directorate


በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በወንጀል ችሎት በሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ በተደረገ ጥናት የግብዓት ማሰብሰቢያ ዉይይት ተደረገ
Selam Warga
/ Categories: News

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በወንጀል ችሎት በሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ በተደረገ ጥናት የግብዓት ማሰብሰቢያ ዉይይት ተደረገ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በወንጀል ችሎቶች የሚታዩ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ዙሪያ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ላይ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም የግብዓት ማሰባሰቢያ ዉይይት ተካሄዷል፡፡

በዉይይቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮችና ዳኞች የተሳተፉበት ሲሆን የስራዉ ዋና ባለቤት የሆኑት ዳኞች በመድረኩ መሳተፋቸዉ በጥናቱ የተለዩ ችግሮችና ማሻሻያ ሃሳቦች ላይ በጋራ በመወያየት የቀረበዉን ጥናታዊ ፅሁፍ መነሻ በማድረግ በቀጣይ መካተት ስላለባቸዉ ተጨማሪ ግብዓቶችንና ሃሳቦች በማሰብሰብ ሰነዱን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ተገኝተዉ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የለዉጥ ስራዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አሰራሮችን በመፈተሽና በማሻሻል እንዲሁም በዳኝነት ስራ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየትና ተገቢዉን እርምጃ በመዉሰድ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ማሳደግና የዳኞችን አቅም የማጎልበት ስራ በሰፊው እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዉ በእለቱ የቀረበው የጥናት ዉጤትም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል ችሎቶች የሚስተዋሉትን ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩን ለማጠናከርና ለማሳለጥ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጥናቱ የተዘጋጀዉ ከሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከተውጣጡ የወንጀል ችሎት ዳኞች ሲሆን ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡር ዳኛ መሃመድ አህመድ፣ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክቡር ዳኛ ጌታሁን ገ/መስቀል እንዲሁም ከፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ክቡር ዳኛ ጥላሁን ሙላት ተሳትፈውበታል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በውይይት መድረኩ ላይ ጥናቱ ተገቢ መሰረት ያለው መሆኑን አንስተው የበለጠ በማዳበር ለትግበራ ብቁ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ፍርድ ቤቶች በየጊዜዉ ለሚሰሯቸዉ የማሻሻያ ስራዎች ግባቸውን እንዲመቱ ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰሩ ስራዎች የህግ ማእቀፍ እንዲኖራቸው ፣ እንዲሁም አንዳንድ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት ጥናቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ፍርድ ቤቶች የህዝብ አመኔታን ያተረፉ እንዲሆኑ ለማድረግ የወንጀል ፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል እንዲሁም ዳኞች እና ፍርድ ቤቶች ያላቸዉን ሚና በማሳደግ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በደረጃ ለመፍታት መሰል ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልፀዋል፡፡

አክለውም ከግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ የተገኙ ሀሳብ አስተያየቶች ታክለውበት ጥናቱ ተጠቃሎ ወደ ድርጊት መርሃ ግብር የሚቀየርና ማሻሻያዎችን በማድረግ የሚሰራበት ይሆናል ብለዋል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው ከአዉሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

Print
151