Temesgen Alemayehu / Monday, June 19, 2023 / Categories: News, CJPO NEWS ተወላጅነትን በማረጋገጥ እና በመካድ ክርክር እንዲሁም በዘረመል ምርመራ አጠቃቀም ላይ የተዘጋጀ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሔደ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተወላጅነትን በማረጋገጥ እና በመካድ ክርክር እንዲሁም በዘረመል ምርመራ አጠቃቀም ላይ ለፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች ያዘጋጀው የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ከሰኔ 10-11 ቀን 2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ተካሒዷል፡፡ በመድረኩ ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተውጣጡ 85 ዳኞች የተሳተፉበት ሲሆን በሕግ ወላጅነትና ተወላጅነት ስለሚረጋገጥባቸው መንገዶች ገለጻ ተደርጓል፡፡ "ተወላጅነትን የማረጋገጥ እና የመካድ ክርክር" በሚል ርዕስ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኑረዲን ከድር ማብራሪያ የቀረቡ ሲሆን ገለጻቸውን ከዓለም አቀፍ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽንና ከአፍሪካ የሕጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር መርሆዎች፣ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት እና ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ድንጋጌዎች ጋር በማዛመድ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽንና የአፍሪካ የሕጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር መሠረት ያደረጓቸው መርሆዎች ከአድልኦ ነጻ የመሆን፣ ለሕጻናት ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ የመስጠት (adherence to the best interest of the child)፣ የሕጻናት የመኖርና በምቹ ሁኔታ የማደግ እንዲሁም የሕጻናት ተሳትፎ መርሆዎች መሆናቸውንና መርሆዎቹ ለማንኛውምና ለሁሉም የሕጻናት መብት ተግባራዊነት መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎችን እንደሚጥሉ ገልጸዋል፡፡ በገለጻቸውም ተወላጅነትንና አባትነትን ለማረጋገጥ መሠረት የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን ያብራሩ ሲሆን ለፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ያገኙ አስተማሪና አከራካሪ ጉዳዮችንም በማቅረብ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገመንግሥት እና ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ አቅርበው በተሳታፊዎችም የሀሳብ ልውውጥ ተደርጎባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ክቡር ዳኛው ተወላጅነትን የመካድ ክስ ለማቅረብ የፍርድ ቤት ፈቃድ በሚያስፈልግበት ሁኔታ ላይ እና የዘረመል-ምርመራ ውጤት ተወላጅነትን ለመካድ በቀረበ ክስ ላይ ስላለው የማስረጃነት ሚና አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኢንስፔክተር ወንድማገኝ ፀጋዬ በዘረ- መል የምርመራ ሳይንሳዊ ሒደት ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በአገራችን የዘረ-መል ምርመራ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አማካኝነት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ከዚህ ጋር በተያያዘ በመሰጠት ላይ የሚገኙ አገልግሎቶችን አብራርተዋል፡፡ የዘረ-መል ምርመራ ውጤትም ሳይንሳዊ ሒደቱን ተከትሎ ከተከናወነ የሚገኘው ውጤት የማያጠራጥርና አስተማማኝ መሆኑን አስረድተው ዘርፉ ተወላጅነትን ለማረጋገጥ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለፎረንሲክ ምርመራ የሚያበረክተውን ጉልህ ሚና ዘርዝረዋል፡፡ በሥራ ላይ የሚፈጠር ጫናን (Stress Management) የተመለከተ ማብራሪያ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ ትምሕርት ክፍል መምሕር በሆኑት በዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ቀርቧል፡፡ በሥልጠናና በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ ተክለሀይማኖት ዳኜ እንደገለጹት ወደፊትም ተመሳሳይ መድረኮች እየተዘጋጁ በተመረጡ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የተሻለ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ዳኞች ሥልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ መድረኩ የተዘጋጀው በዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ (UNFPA) እና በሕጻናት አድን ድርጅት (Save the children) የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ታውቋል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት የተደራጀው የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከል ተመርቆ ተከፈተ Next Article በቤተሰብ አስማሚነት ላይ የተዘጋጀ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሔደ Print 2872