Welcome to Child Justice Project Directorate


የህጸናትን መብት እና የላቀ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና የመስማማት ክህሎት ላይ  2ተኛ ዙር ስልጠና ተሰጠ
Selam Warga
/ Categories: News, CJPO NEWS

የህጸናትን መብት እና የላቀ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና የመስማማት ክህሎት ላይ 2ተኛ ዙር ስልጠና ተሰጠ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከUNFPA እና Save The Children International ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የህጻናትን መብት እና የላቀ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና የማስማማት ክህሎት ላይ ለዳኞች ፤ረዳት ዳኞች እና የሶሻል ወርክ ባለሙያዎች የካቲት 27 እና 28 ቀን 2018 ዓ.ም 2ተኛ ዙር ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ ቤተሰብ የማህበረሰብ ብሎም የሀገር መሰረት መሆኑን እና ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ይህን እንደ ተቋም ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ፍ/ቤቶች ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

አክለውም የቤተሰብ ጉዳይን በተመለከተ የፍርድ ቤት መር አስማሚ ስርአትን ተግባራዊ በማድረግ ህጻናትን የተመለከቱ ጉዳዩች አፋጣኝ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ቆጣቢ፣ ፍትሃዊ እና ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት /Court Annexed Mediation/ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመሪያ ወጥቶለት፣ በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተዋቅሮ በስፋት እየተተገበረ መሆኑን የተሻሻለውን የቤተሰብ ህግ፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያን እና ህገ መንግስቱን በመጥቀስ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ጋብቻ/ቤተሰብ/ እንዳይፈርስ ጥበቃ ማድረግ የወደፊት ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናትን ደህነት፣ መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ በመሆኑ እና ፍቺን ማስቀረት ባልተቻለ ጊዜም የልጅ አስተዳደግን የተመለከቱ ጉዳዮች በስምምነት ማለቃቸው የህጻናትን የላቀ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚረዳ በመሆኑ ፍ/ቤት መር የማስማማት ሂደት ከህጻናት መብት ጥበቃ አንጻርም ሚናው የጎላ እና በተጠናከረ መልኩ ሊተገበር የሚገባ ነው ብለዋል። ለውጤታማነቱም የባለሞያዎችን አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስልጠናው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ክቡር ዳኛ ቀንዓ ቂጣታ እና የሶሻል ወርክ ባለሞያ እና የቤተሰብ ጉዳይ አማካሪ እንዲሁም አስማሚ በሆኑት ዶ/ር አለምሸት መኮንን የተሰጠ ሲሆን በስልጠናውም ፍርድ ቤት መር አስማሚነት በጠቅላላው እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ከህፃናት መብት ጥበቃ አንጻር ያለው ፋይዳ እና የህግ ማእቀፍ፣ የሌሎች ሃገራት ተሞክሮ፣ ጠቀሜታዎቹ ፣ነባራዊ አተገባበሩ፣ ሊስተዋሉ ሚገባቸው የሙያዊ ስነምግባር መርሆች እና አስፈላጊ ክህሎቶች የተዳሰሱ ሲሆን ተሳታፊዎች በተግባር በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ በስልጠናው የተነሱ ነጥቦችን አዳብረዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያም የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክተር የሆኑት ክብርት ዳኛ ህውስት አሸናፊ ሰልጣኞች በሁለቱ ቀናት የስልጠና ሂደት ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት የማስማማት ስራ በሚከውኑበት ወቅት በመተግበር በውሳኔዎቻቸው የህጻናትን የላቀ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ያለባቸውን የህግ እና የሞራል ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በማጠቃለያቸውም ህጻናትን በተመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ መስጠት ወደፊት የሃገርን እጣ ፈንታ ከመወሰን ጋር የሚስተካከል በመሆኑ ሁሉም የተጣለበትን ሃላፊነት እንደሚወጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

Previous Article በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ከተገኙ ህጻናት እንዲሁም በሴቶች እና ህጻናት ችሎት ለሚሰሩ የፌዴራል ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
Print
443