Selam Warga / Monday, August 19, 2024 / Categories: News, CJPO NEWS ፍርድ ቤቱ የህጻናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያና የዳኞች ለህጻናት ተስማሚ ፍትህ የስልጠና ማንዋልን አስመረቀ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የህጻናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያና የዳኞች ለህፃናት ተስማሚ ፍትህ የስልጠና ማንዋልን ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የህፃናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያ ወላጆች በፍቺና በተለያዩ ምክንያቶች በሚለያዩበት ወቅት ህፃናቱ በሚገጥሟቸዉ ቀለብ የማግኘት መብት አተገባበር ክፍተት የሚሞላ እንደሚሆን ገልፀዉ ሌላኛዉ ለህፃናት ምቹና ተስማሚ የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋትና የህፃናቱን ጉዳይ ለሚመለከቱ ዳኞች አቅም ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀዉ የዳኞች የስልጠና ማንዋል ለህፃናት ተስማሚ ፍትህን የተመለከቱ በኢትዮጵያ የፀደቁ አለም አቀፍ እና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፣ሰነዶችና ህግጋቶች ወጥ በሆነ መንገድ እንዲተገበርና እንዲከበር ያስችላል ብለዋል፡፡ ክብርት ፕሬዝዳንቷ አክለውም ለምርቃት የቀረቡት ሰነዶች የፍርድ ቤቱን የተገልጋይ ተኮር አሰራርን ከማሳደግ በተጨማሪ በፍትህ ስርዓቱ ለሚያልፉ ህፃናት መብትና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የህጻናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እትመት አሰፋ እና ጠበቃ ጌዲዎን ሲሳይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የዳኞች ለህፃናት ተስማሚ ፍትህ የስልጠና ማንዋልን በተመለከተ በዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ እና ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ ገለፃ ተደርጎባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት የ2016 በጀት ዓመት ቁልፍ ተግባራት በህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳኛ ተክለሐይማኖት ዳኜ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ሰፊ ዉይይት፣ ሃሳብ አስተያየት ከተሳታፊዎች የተሰጠባቸው ሲሆን ሰነዶቹን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለዩኒሴፍ ኢትዮጵያ፣ ክብርት ዳኛ እትመት አሰፋ፣ አቶ ደሳ ቡልቻ፣ ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ፣ ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ እና ጠበቃ ጌድዮን ሲሳይ የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቷል፡፡ በመጨረሻም የቀለብ አወሳሰን መምሪያውን በመጠቀም ዳኞች የቀለብ ክርክሮችን ወጥ፣ተገማች እንዲሁም ቀልጣፋ እንዲያደርጉ የተጠቆመ ሲሆን ለተግባራዊነቱም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡ Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአፍሪካ ህብረት በህጻናት ጥበቃ ጉዳዮች እና ሌሎች ጎጂ ተግባራት በኢትዮጵያ ሀገራዊ የክትትል ተልዕኮ ወርክሾፕ ላይ በመገኘት ሪፖርት አቀረበ Next Article በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብቶች ኮሚቴ አማካኝነት እየተዘጋጀ ባለው General Comment 27 on Access to Justice for children ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ Print 646