Welcome to Child Justice Project Directorate


ፍ/ቤቶች የሕጻናትን መብቶችና ጥቅሞች ከማስከበር አንጻር ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኝ ተጠቆመ
Temesgen Alemayehu
/ Categories: News, CJPO NEWS

ፍ/ቤቶች የሕጻናትን መብቶችና ጥቅሞች ከማስከበር አንጻር ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኝ ተጠቆመ

የፌደራል ፍ/ቤቶች የሕጻናትን መብቶችና ጥቅሞች ከማስከበር አንጻር ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ገለጹ፡፡
ክብርት ፕሬዚደንትዋ ይህን የገለጹት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (UNICEF) ጋር በመተባበር ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ 180 ያህል ዳኞች “ሕጻናት ተኮር የፍትሕ ሥርዓት መገንባት” በሚል ርዕስ በቢሾፍቱ ከተማ ግንቦት 26 እና 27 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሔደውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
የሕጻናትን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር በፌደራል ፍ/ቤቶች ከተደረጉት ጥረቶች አንዱ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚያልፉ ሕጻናት በዕድሜያቸው ለጋነትና ለጥቃት ተጋላጭነት ምክንያት የተለየ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤትን ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በማቋቋም በሕጻናት ፍትሕ አስተዳደር ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ አካል እንዲኖር መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሕጻናት ጉዳይ ላይ ትኩረት በመስጠት ሕጻናት በተጠቂነት፣ በምስክርነት፣ በወንጀል ድርጊት ውስጥ በመግባት እንዲሁም በቤተሰብና በልዩ ልዩ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ጥቅምና ደሕንነታቸው በተሻለ ሁኔታ የሚጠበቅበትን አሠራር እውን ለማድረግ በፍ/ቤቶች የማሕበራዊ ሳይንስ ክፍል ተቋቁሞ ለሕጻናት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝና ይህም በሰፊው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በተመሳሳይም ፍትሕ ለሕጻናት ተደራሽ እንዲሆን ታስቦ የመክፈል አቅም የሌላቸው ሕጻናት ተገቢውን የሕግና ሌሎች የማሕበራዊና ሥነልቦናዊ አገልግሎቶችን አግኝተው ሁለንተናዊ ፍትሕ እንዲያገኙ ለማስቻል ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ሕጻናትና ቤተሰቦቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው የፌደራል ፍ/ቤቶችም በዚህ የሥራ ትስስር ውስጥ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው “የሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ቀደምትነት መርህ ትርጓሜና አተገባበር (The Principle of the Best Interest of the Child)”፣ የሕጻናት መብት እና ደሕንነትን በማስከበር ሒደት የማሕበራዊ ሳይንስ ባለሙያ ተግባር እና ሚና እንዲሁም የሕጻናት መብቶች ስምምነት አተገባበር በኢትዮጵያ በሚሉ ርዕሶች ላይ ተሰጥቷል፡፡
“የሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ቀደምትነት መርህ ትርጓሜና አተገባበር (The Principle of the Best Interest of the Child)” በሚል ርዕስ ማብራሪያ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ ሲሆኑ የሕፃናት መብቶች ጠቅላላ መርሆች፣ ለሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ የመስጠት መርህ ምንጮች፣ ለሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ የመስጠት መርህ መነሻዎች እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሕጻናትን በሚመለከት ከወጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንጻር አብራርተዋል፡፡
“የሕጻናት መብት እና ደሕንነትን በማስከበር ሒደት የማሕበራዊ ሳይንስ ባለሙያ ተግባር እና ሚና“ በሚል ርዕስ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ መምሕር በሆኑት በዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ህጻናት እራሳቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን የመግለጽ መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ በማንኛውም ምክንያት አድልኦ ሊደረግባቸው እንደማይገባ፣ የማሕባራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች የሥነምግባር ኃላፊነት፣ በሕጻናት ሥነሕይወታዊ፣ ማሕበራዊና መንፈሳዊ የዳሰሳ ጥናት አካሔድ፣ በዳሰሳ ጥናት ዘዴዎች እና ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
“የሕጻናት መብቶች ስምምነት አተገባበር በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የምርምርና ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ አሮን ደጎል የቀረበው ማብራሪያ አገራችን የተቀበለቻቸውን ሕጻናትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተመረጡና ሕጻናትን ከተመለከቱ የሰበር ውሳኔዎች ጋር በማዛመድ ምልከታቸውን ያቀረቡበት ነበር፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Next Article በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት የተደራጀው የሕጻናት ማስመስከሪያ ማዕከል ተመርቆ ተከፈተ
Print
2337