/ Categories: CASSATION, Judgement, 2013, Cassation

እነ አቶ ጁሀር ያህያ እና ወ/ሮ መሬም አህመድ የሰ.መ.ቁ 179607

ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሊቀርብ የቻለው አመልካቾች የአማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ 03-76478 በ15/8/11ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት በ16/12/11ዓ.ም በተጻፈ የተሻሻለ የሰበር አቤቱታ ስላቀረቡ ነው፡፡የጉዳዩ አመጣጥ የአሁን 1ኛ ተጠሪ በስር የአብክመ ጎንደር ዞን አስተዳደር የጎንደር ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት በአሁን 2ኛ ተጠሪ ላይ ባቀረቡት ክስ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር በ1960ዓ.ም ተጋብተን 4 ልጆች ወልደን ንብረት አፍርተን ስንኖር ባለመግባባታችን ጋብቻው ሳይፈርስ ተለያይተን ኖረናል፡፡ ስለሆነም አሁን ጋብቻው ፈርሶ 2ኛ ተጠሪ ሌላም ሚስት ስላለው የዘረዘርኩትን ንብረት ለሶስት እንድንካፈል በማለት ዳኝነት ጠይቀው 2ኛ ተጠሪም ባቀረቡት መልስ 1ኛ ተጠሪ ልጅ ወልዳልኛለች እንጂ ጋብቻ የለንም በማለት ተከራክረው ፍ/ቤቱም ጋብቻ አለ የለም? የሚለውን በምስክር እና በሰነድ በማረጋገጥ ጋብቻ እንዳለ በማረጋገጥ ብይን ሰጥቶ 1ኛ ተጠሪ የዘረዘሩትን ንብረቶች ባልና ሚስት የሆኑት 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች እንዲሁም በስር 1ኛ ጣልቃገቦች የነበሩት የአሁን አመልካቾች እንዲካፈሉ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ክልሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሄዶ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ በ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ መካከል ጋብቻ ያለ መሆኑን አረጋግጦ የአሁን 3ኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብተው ባለመከራከራቸው የተነሳ የስር የወረዳ ፍ/ቤቱን ውሳኔ በመሻር የአሁን 3ኛ ተጠሪ ጣልቃገብተው እንዲከራከሩ ውሳኔ በመስጠት ጉዳዩን ለስር የወረዳው ፍ/ቤት በመለሰው መሰረት 3ኛ ተጠሪ በስር የወረዳው ፍ/ቤት 2ኛ ጣልቃገብ ሆነው ባቀረቡት  የጽሁፍ ክርክር የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበው በፍሬጉዳዩ ላይ ባቀረቡት መልስ 1ኛ ተጠሪ ዘርዝራ ያቀረበችው ንብረት እንዲፈራ ያደረገችው አስተዋጽኦ የለም፤ በ2ኛ ተጠሪ እና በ3ኛ ተጠሪ ጥረት የተፈሩ ንብረቶች ናቸው፤ በ1ኛ ተጠሪ ክስ በተራ ቁጥር 2 ላይ  የተጠቀሰው እና አሁን አመልካቾች በዚህ ፍ/ቤት ላቀረቡት የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው አከራካሪው በመሀል አራዳ የሚገኘው ባለሁለት ፎቅ ቤት ከአሁን አመልካቾች ልጆቻችን(በስር ከ1ኛ ጣልቃገቦች) ጋር በሽርክና ስራ ከመጀመራችን በፊት በንጉሱ ዘመን ከቀበሌ የተቀበልነው እኔ እና 2ኛ ተጠሪ ስንሆን እስከ 1983ዓ.ም በመኖሪያ ቤት የምንጠቀምበት 2ኛ ተጠሪ እና እኔ ባለቤቱ 3ኛ ተጠሪ ስንሆን 2ኛ ተጠሪ በእርጅና ምክንያት ስራ ሲያቆም ለገቢ ምንጭ እንዲሆነን ከጋራ ልጆቻችን ጋር የሽርክና ውል ወስደንበታል፡፡ ፎቁም የተሰራው በልጆቻችን ጥረት በመሆኑ የልጆቻችን የ60% ድርሻ መኖሩን ስለማውቅ በነሱ በኩል የቀረበውን የጣልቃገብነት አቤቱታ አልቃወምም፤ ነገር ግን ፍ/ቤቱ በ2ኛ ተጠሪ እና በአሁን አመልካቾች(በስር 1ኛ ጣልቃገቦች) መካከል የተደረገው የሽርክና ውል ፈራሽ ነው የሚልበት ምክንያት ካለው ክፍፍልን በተመለከተ የቤቱ እና ቦታው ግማሽ ሀብት የ3ኛ ተጠሪ በመሆኑ ግማሽ ባለሀብት ናት ይባልልኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡

Previous Article እነ ወ-ሮ የሺወርቅ ፈንታዉ እና ወ-ሮ ፀሀይነሽ ፈንታዉ የሠ-መ-ቁጥር 190450
Next Article አቶ ቀኖ ኩታሳ እና ወ-ሮ መሳይ ገመቹ የሰ-መ-ቁ 180936
Print
15245