ጉዳዩ የጋራ የሆነ የእርሻ መሬት በሽያጭ ለማስተላለፍ የተደረገ ነዉ የተባለዉ ዉል ቀሪ እንዲደረግና ይዞታዉን ለማስለቀቅ እንዲሁም አላባ ለማስከፈል የቀረበ ክስ የመዳኝት ሥልጣን የሚመለከት ነዉ፡፡ አመልካች በተጠሪዎችና በስር 1ኛ ተከሳሽ አቶ ሙስጠፋ ዩሱፍ ላይ በሐረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ ከስር 1ኛ ተከሳሽ ጋር ለ30 ዓመታት በትዳር ተሳስረን አብረን ስንኖር በሐረር ክልል በድሬ ጠያራ ወረዳ በአቦከር ሙጢ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ዉስጥ ያለንን አንድ ጥማድ ከግማሽ የሆነ አዋሳኙ በክሱ የተጠቀሰዉን የእርሻ መሬት ያለእኔ ፈቃድ በሕገ-ወጥ መንገድ ለአሁን ተጠሪዎች በሽያጭ አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአመት 20 ኩንታል ማሽላ በማምረት ማግኘት የምንችለዉን በኩንታል በብር 1200.00 ሂሳብ ብር 24,000.00 አሳጥዉኛል፡፡እየተቃወምኩ በመሬቱ ላይ ተጠሪዎች ቤት ሰርተዉበታል፡፡ስለሆነም ዉሉ ሕገ-ወጥ ስለሆነ እንዲፈርስና የገነቡትን ቤት አፍርሰዉ ይዞታዬን እንዲለቁ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡……………