ይህ የወጪና ኪሳራ፣ የተቋረጠ ገቢን የሚመለከት ክርክር የተጀመረዉ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲሆን፣ የአሁን አመልካች የሥር ተከሳሽ፣ የአሁን ተጠሪ የሥር 1ኛ ከሳሽ፣ በዚህ ችሎት የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነዉ መርጌታ ታዬ ሉሉ ሌሎች የሥር 2ኛ ተከሳሽ ሆኖ ሲከራከሩ ነበር። ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.300510 በ02/11/2011 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት በማመልከታቸዉ ነዉ።
የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ በሥር ከሳሾች እና በሥር ተከሳሽ መካከል የነበረዉን የወጪና ኪሳራ እንዲሁም ከቤት ጋር በተያያዘ የተቋረጠ ገቢን የሚመለከት ክርክር የሥር የከፍተኛ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ ዉሳኔ ከሰጠ በኋላ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.208 መሰረት የቀረበዉን አቤቱታ ተከትሎ ጉዳዩን ድጋሚ በማየት በመ.ቁ.61826 በ16/9/2010 ዓ.ም በሰጠዉ ዉሳኔ የሥር ተከሳሽ በክርክሩ ምክንያት በሥር ከሳሻ ላይ ለደረሰዉ ወጪና ኪሳራ ብር 210.00 [ሁለቶ አስር] እንዲከፍላት፤ የታጠዉን የቤት ኪራይ ገቢን በተመለከተ የተጠየቀዉ ዳኝነት የክስ ምክንያት ስለሌለዉ ዉድቅ ነዉ በማለት ወስኗል። የሥር 1ኛ ከሳሽ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበች ቢሆንም ፍ/ቤቱ ይግባኙን በትዕዛዝ ዉድቅ በማድረግ የሥር ፍ/ቤት ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የሥር ከሳሽ አሁንም በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበች ሲሆን ችሎቱም ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ የሥር የከፍተኛዉ ፍ/ቤት የሥር ተከሳሽ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.208 መሰረት ያቀረበዉን አቤቱታ ተቀብሎ የቀደመዉን ዉሳኔ በመሻር የሰጠዉ ዉሳኔ የሕግ ድጋፍ የለዉም በማለት በመሻር ወስኗል። የአሁን ሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ። የአሁን አመልካች ባቀረበዉ የሰበር አቤቱታ፡ ግራ ቀኙ አንድ ክልል ነዋሪዎች በመሆናችን የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን ጉዳይ ለማየት ስልጣን እንደሌለዉ የአሁን አመልካች ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረበዉ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አንሶቶ ነበር። የሥር የክልሉ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ሆነ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ጉዳይ ያዩት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 [2፣ 4] መሰረት በተሰጠዉ የዉክልና ስልጣን በሆኑ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ ቅሬታ መቅረብ ያለበት በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 [1] መሰረት ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ሆኖ ሳለ የሥር የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን መቃወሚያ በዝምታ በማለፍ የሰጠዉ ዉሳኔ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.244 [1] እና በዚህ ችሎት ከተሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሚቃረን ነዉ። ስለሆነም የሥር የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን ጉዳይ በሰበር አይቶ ለመወሰን ስልጣን ሳይኖረዉ የሰጠዉ ዉሳኔ ሕጋዊ መሰረት የሌለዉ ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት በዝርዝር አመልክቷል።...........