ጉዳዩ የውል አለመፈጸምና የኪሣራ አከፋፈልን የተመለከተ ክርክር ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሠጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ የክርክሩን አመጣጥ ከስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ እንደተረዳነው አመልካች ከሳሽ ሲሆን ተጠሪዎች ተከሳሾች ነበሩ፡፡ አመልካች ግንቦት 04 ቀን 2009 ዓ/ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ ያቀረበው ክስ የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከ2ኛ-8ኛ ተጠሪዎች አባት የሆኑት አቶ ቅጣው መሸሻ ከአመልካች ጋር በተደረገ የንግድ ቤት ኪራይ ውል በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 05 ቀበሌ 12 የቤት ቁጥሩ 1165 የሆነ የንግድ ቤት በወር ብር 212.50 እየከፈሉ ከ1969 ዓ/ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስ እየከፈሉ ሲጠቀሙበት ቆይተው የተከራዩትን ቤት ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከአከራዩ ዕውቅና ውጪ ለሦስተኛ ወገን አከራይተው የማይገባ ጥቅም በማግኘታቸው ምክንያት አመልካች የኪራይ ተመኑን በማስተካከል በወር ብር 31,479.00 እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ አቶ ቅጣው ቅሬታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በዚህ መካከል አቶ ቅጣው መሸሻ ውል ሳያድሱ ሕዳር 13 ቀን 2005 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ 1ኛ ተጠሪ ውል ያላደስነው ባለቤቴ ሕመም ላይ ስለቆየና ሞግዚትነትና ወራሽነት እስከምናረጋገጥ ድረስ ስለሆነ ጊዜ እንዲሰጠን በማለት በጽሁፍ አመልክተዋል፤ ውዝፍ ዕዳውን በተመለከተ የአንድ ዓመት የመክፈያ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ከአመልካች ጋር የውል ሥምምነት አድርገዋል፡፡ በሥምምነቱ መሠረት ዕዳውን መክፈል ጀምረው ያቋረጡ ሲሆን እስከ ታህሳስ 17 ቀን 2009 ዓ/ም ድረስም ሲገለገሉበት ቆይተዋል፡፡ ስለሆነም የኪራይ ገንዘብ ብር 2,311,503.59 ተጠሪዎች ከወለድ ጋር እንዲከፍሉ ሲል ዳኝነት ጠይቋል፡፡………………..