የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 261471 ግንቦት 17ቀን 2013 ዓ/ም የአመልካቾችን ይግባኝ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት መሰረዙ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ተብሎ እንዲታረምላቸው አመልካቾች በመጠየቃቸው ነው፡፡ ጉዳዩ የመፋለም ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩ በተጀመረበት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ አመልካች 1ኛ ተከሣሽ፣ ወ/ሮ አሰገደች ዝናቡ 2ኛ ተከሣሽ፣ 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች ጣልቃ ገቦች ተጠሪ ደግሞ ከሣሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡
ተጠሪ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የተሻሻለ ክሱ በመምህርነት ሲያገለግል ከነበረበት ወለጋ ሲመልስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የቤት ቁጥር 889 የሆነና በደብተር ቁጥር 5/25444 የተመዘገበውን ቤቱን የያዘበትን 1ኛ አመልካች ቤቱን እንዲያስረክበው ሲጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆኑ አቤቱታውን ለጠቅላይ ዐ/ሕጉ አቅርቦ አንደኛ አመልካች ሰኔ 12ቀን 1982ዓ/ም በተፃፈ ለጠቅላይ ዐ/ሕግ በሰጠው መልሱ ቤቱን ለተጠሪ ለማስረከብ ከ50 በላይ ጠያቂዎች በመኖራቸው እንዲሁም ሁለተኛ ተከሣሽ በቤቱ ከ14 ቤተሰቦች በላይ የሚያስዳድሩበት መሆኑን በመግለፅ በቅደም ተከተል እንደሚያስተናግደው ከገለፀ በኋላ እስካሁን ድረስ ቤቱን ያልመለሰለት መሆኑን በመዘርዘር ምንም መብት ሣይኖራቸው የያዙበትን ቤት ለቀው እንዲያስረክቡት የተሰበሰበው ኪራይና ክሱ ከቀረበበት ጊዜጀምሮ 2ኛ ተከሣሽ ኪራይ እንዲከፍሉት እንዲወሰንባቸው ጠይቋል፡፡……………….