ይህ የፍቺ ክርክር የተጀመረዉ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን፣ የአሁን አመልካች እና የአሁን ተጠሪ ሆኖ ሲከራከሩ ነበር። ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.251802 ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልን በማለት በማመልከታቸዉ ነዉ።
የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ የአሁን አመልካች በሥር ፍ/ቤት ባቀረበችዉ ክስ ከተጠሪ ጋር ግንቦት 12 ቀን 2001 ዓ.ም በግብጽ ሀገር ጋብቻ ፈጽመን አብረን ሲንኖር ህጻን ሊና ቴዎድሮስ የተባለችዉን ልጅ የወለድን ቢሆንም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ግንኙነታችን ተቋርጦ በጋብቻ መቀጠል ስላልቻልን ጋብቻችን እንዲፈርስልን በማለት ዳኝነት ጠይቃለች፡፡
የአሁን ተጠሪ በዚህ ክስ ላይ ባቀረበዉ መልስ ከአመልካች ጋር ጋብቻ አልፈጸምንም፣ በጋብቻ ሰነዱ ላይም አልፈረምኩም፣ አመልካች ጋብቻ እንደሌላቸዉ ስለመሆኑ ማስረጃ ተሰጥቷል፤ በግብጽ አገር ጋብቻ የሚፈጸመዉ በፍ/ቤት ነዉ፤ ከአመልካች ጋር በነበረን የግብረ ስጋ ግንኙነት የተጠቀሰችዉን ልጅ ከመዉለዳችን ዉጭ በጋብቻም ሆነ ጋብቻ ሳይፈጽም እንደባልና ሚስት አለመኖራቸዉን ገልጸዉ ጋብቻ በሌለበት የቀረበዉ ክስ ተቀባይነት የለዉም በማለት ተከራክሯል፡፡………………….