የሰበር አቤቱታው ሊቀርብ የቻለው አመልካቾች የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ በሐረሪ ህዝብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መ.ቁ. 05450 የካቲት 01 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠውን ብይን፤ በማጽናት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መ.ቁ. 00159 የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት አቤቱታ በማቅረባቸው ነው፡፡
ጉዳዩ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በሐረሪ ህዝብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የአሁን ተጠሪ በአሁን አመልካቾች ላይ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ይዘት በአጭሩ፡- የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31(1) እና (2) በመተላለፍ አመልካቾች የእምነት ማጉደል ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡ የአሁን አመልካቾች ክሱን በሚመለከት ያቀረቡት መቃወሚያ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 78(2)፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጀ አዋጅ ቁጥር 322/96 አንቀጽ 2 እና በአዋጅ ቁጥር 434/97 መሰረት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም፤ አመልካቾች እምነት አጉድለዋል የተባለበት የግል የጤና አገልግሎት ከሚሰጥ ድርጀት ጋር በተያያዘ እንጂ የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የመንግስት የልማት ድርጅት ባለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 ስር ክስ ሊቀርብ አይገባም በማለት ከክሱ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡………