ጉዳዩ የቤት ሽያጭ ውል አፈጻጸምን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ በመጀመሪያ በታየበት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ደግሞ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ አመልካች በተጠሪ ላይ በመሰረቱት ክስ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የቤት ቁጥሩ አዲስ የሆነውን በ360 ካሬ ሜትር የሰፈረ ቤት በብር 650,000.00 ከተጠሪ ገዝቻለሁ፡፡ በውሉ ላይ ተጠሪ ቤቱን እንዳስረከቡ የተገለጸ ቢሆንም ቤቱን በምረከብበት ወቅት እናቴ ከዚህ አለም በሞት የተለየች በመሆኑ ችግር ስለገጠመኝ ሳልረከብ የቀረሁ ስለሆነ ሀዘኔን ጨርሼ ተጠሪ ቤቱን እንዲያስረክቡኝ ብጠይቅም ቤቱን ሊያስረክቡኝ ፈቃደኛ ስላልሆኑ ቤቱን እንዲያስረክቡኝ እና በዉሉ የተመለከተዉን መቀጫ ብር 100,000.00 እንዲከፍለኙ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ተጠሪ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በማስቀደም ፍሬ ነገሩን በተመለከተ በሰጡት መልስ አመልካች ከተጠሪ ጋር ፈጸምኩኝ ያሉትን ወል አልፈጸምኩም፡፡ምንም ገንዘብ አልተቀበልኩም፡፡አመልካች ፈጸምኩኝ ያሉት ዉል በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1723/1 መሰረት ያልተፈጸመና ሕጋዊ መሰረት የሌለዉና በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1720/1 መሰረት ረቂቅ ነዉ፡፡ ከአመልካች ጋር ቤተሰባዊ ግንኙነት ስለነበረኝ ጉዳይ እንዲያስፈጽሙልኝ የዉክልና ሥልጣና በርካታ ሕጋዊ ሰነዶችን ሰጥቻቸዉ በእጃቸዉ የሚገኝ ቢሆንም አመልካች ዉል አለኝ የሚሉት ዉል ሳይኖርና የተቀበልኩት ገንዘብ ሳይኖር በሀሰት የቀረበ ስለሆነ ክሱ ዉድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡……..