ስለ ፍርድ አፈጻጸም (ABOUT US)
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት በሁሉም ደረጃ ባሉ በፌ/ፍ/ቤቶች የተሰጡትን የፍታብሄር ፍርዶች የሚያሰፈጽም፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የተደራጀ የስራ ክፍል ነው፡፡ በሀገራችን ባለው የፍታብሄር የፍትህ አስተዳደር ስርዓት ፤ ፍርድ የሚፈጸመው ፍርዱን በፈረደው ፍ/ቤት ወይም እንዲያስፈጽም በታዘዘው ፍ/ቤት አማካኝነት ነው። ይሁንና በፌደራል ፍርድ ቤቶች ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፍርዶች ሁሉ በፍርድ ቤቶች ብቻ ሊፈጸሙ የማይችሉ በመሆናቸው ፍ/ቤቶች በቀጥታ በራሳቸው የሚያስፈጽሟቸውን ጉዳዮች በቀጥታ ትዕዛዝ በመስጠት የሚያስፈጽሙ ሲሆን የቴክኒክ ሙያ እና ዕገዛ የሚጠይቁትን ጉዳዮች በተመለከተ ዳኞች እየለዩ ፍርድ አፈጻጽም ዳይሬክቶሬት እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ይሰጣሉ።
በዚህም መሰረት የቴክኒክ ሙያ የሚፈልጉ ፍርዶችን በሚመለከት ለምሳሌ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት መገመት፣ ንብረት ማስረከብና መረከብ ፣ፍርድ ያረፈባቸውን ንብረቶች በፍ/ቤት ውሳኔ መሰረት መሸጥ፣ የሒሳብ ሰንድ አዘጋጅቶ ክፍያ መፈጸም እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚፈጸሙት በዚሁ የሥራ ክፍል ነው ። የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት እንዲሁም በዚሁ የሥራ ክፍል የተደራጁ የስራ ክፈሎችና ባለሙያዎች ለሁሉም ፍ/ቤቶችና ችሎቶች ሰለ አከናወኑት የፍርድ አፈጻጸም ሁኔታና ስለገጠማቸው ተግዳሮቶች የአፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ፍ/ቤቶች ትዕዛዝ እንዲሰጡት ያደርጋሉ።
ፍ/ቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነትም ሆነ በባለጉዳዮች አቤቱታ አቅራቢነት ልዩ ልዩ የፍርድ አፈጻጸም የሰራ ክፍሎችና ባለሙያዎች ያከናወኑትን ተግባር ሪፖርት እንዲያቀርቡ፣ ችሎት ቀርበው እንዲያስዱ ፣ከሀራጅ ሽያጭ ተራፊ ገንዘብ መኖር አለመኖሩን እንዲያሳውቁ እና አጠቃላይ የባለሙያዎችን የፍርድ አፈጻጸም ሂደት ሁሉ እየገመገሙ ትዕዛዝ የሚሰጡበት አሰራር በልምድ የዳበረ ነው ።
የፍርድ አፈጻጸም አደረጃጀት የሠው ሀብትና ንብረት አስተዳደርን በተመለከተ የሥራ ክፍሉ አስቀድሞ በመዋቅር በዳይሬክቶሬት ደረጃ በጠቅላይ ፍ/ቤት ስር የተደራጀ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 መሰረት ተጠናክሮ በጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲተዳደርና እንዲጠናከር በህግ የተመለከተ የሥራ ክፈል ሲሆን ዳይሬክቶሬቱ በዋናነት ተግባሩን ዕለት በዕለት የሚያከናውነው በፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ውሳኔዎች እና የፍ/ሥ/ህጉን መሰራታዊ መርሆዎችን ተከትሎ ፍርዱን የሚያስፈጽም ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጠው የሥራ ከፍል ነው ።