ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ እየተካሄደ ይገኛል
/ Categories: News

ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ እየተካሄደ ይገኛል

የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን ያካተተ ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ በቀን 27/07/2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ነፃ፣ ገለልተኛ እና የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ሥርዓት መኖር ለሀገር መረጋጋት፣ መጽናት እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ይህን ሃላፊነትን በመሸከም ፍርድ ቤቶች በጋራ በትብብር መንፈስ በመስራት ቀጣይ ስራዎች ላይ ለመምከርና መልካም ተሞክሮዎች ለመጋራት እንዲሁም የሕግ የበላይነትና ፍትሀዊነት በሚረጋገጥባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ለማካሄድና እና አፈጻጸማቸውን ለመከታተል ይህ ሀገር አቀፍ መድረክ አጋዥ በመሆን የዳኝነት አካሉ በአገልግሎት ደረጃ የላቀ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል፡፡

አክለውም የፌደራል ሕጎች በክልል ደረጃ የተቀራረበ አተረጓጎም እንዲኖራቸው ምክክር ማድረግ እንዲሁም የፌደራል ሕጎች በክልል ያላቸውን አተገባበር መገምገም እና ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ለዛሬ መድረክ የተመረጡ አጀንዳዎች የክልል ፍርድ ቤቶች በውክልና ለሚሰጡት የፌደራል የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ የድጎማ በጀት ድልድል የሚመራበት አፈጻጸም ማኑዋል የሚዘጋጅበት ሁኔታ፣ ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች ግንኙነት መድረክን ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ የሚያስተባብረው ጽ/ቤት መዋቅር እና የሰው ሀይል አደረጃጀት፣ የዳኝነት አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ መተግበር ስለሚቻልበት ሁኔታ እና ለሁሉም ፍርድ ቤቶች የጋራ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡

Previous Article በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ አምባሳደር ክቡር ሚ/ር አሌክስ ላሜክ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Next Article በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ የጋራ አቋም በመያዝ ተጠናቋል።
Print
222