Monday, December 23, 2024 / Categories: News ሀገር አቀፍ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ ለሁለት ቀናት ሲደረግ የቆየው ሀገር አቀፍ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ በቀን 11/04/2017 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ በመድረኩም ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ፍትህ ሚኒስቴር እና ክልል ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የህግ የበላይነት፣ የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም እንዲሁም አለምአቀፍ የአቃቤ ህግ መድረክ ተሞክሮ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስተር ክብርት ወ/ሮ ሃና ዓርአያስላሴ፣ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን እና በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የፍርድ ቤቶች ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጂክ ስራ አመራር ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤል ጌትነት የቀረበ ሲሆን በቀረበው ገለጻ ከዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነት፣ ውጤታማ አገልግሎት ከመስጠት፣ ከተደራሽነት እና ቅንጅታዊ አሰራር አኳያ በፌ/ፍ/ቤቶች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የተዳሰሱ ሲሆን በተጨማሪም የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ከማምጣት እና ይህንኑ ቴክኖሎጂ በክልል ፍርድ ቤት ከማስፋፋት አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የገንዘብ መዋጮ አወሳሰን እና አተገባበር ላይ ከአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ፣ የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን በተፋጠነ እና ተጎጂ ተኮር በሆነ መንገድ ለመዳኘት የተዘጋጀ ሰነድ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክቡር ዳኛ መላኩ ካሳዬ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ አማራጭ ቅጣት ተሞክሮ በደቡብ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት በክቡር አቶ አንዱአለም አምባዬ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ቀርቦ የጸደቀ ሲሆን ከክልሎች የሚመረጡ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን አስመልክቶ እጩዎች ቀርበው ምርጫ ከተደረገ በኋላ ከክልል የዳኝነት አካላት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቆጭቶ ገ/ማርያም፣ ከክልል ፍትህ ተቋማት የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊ ክቡር አቶ ማቶ ማሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡ በመጨረሻም ለደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ለደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም ለጋሞ ዞን አስተዳደር የምስጋና ምስክር ወረቀት ከክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትና ከክቡር ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ተበርክቷል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የፍትህ አካላት የተሻለ ፍትህ፣ ሰላም እና ብልጽግና እንዲኖር የጋራ ተልዕኮ በመያዝ በተሻለ አጀንዳና ዘላቂ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዬች ላይ በመወያየት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አንስተው መድረኩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን አስተዋጽኦ ላደረጉት ለክልሉ መንግስት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ለጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ እንዲሁም ለተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ከሰአት በሚኖረው መርሃ ግብር የህግ ተርጓሚዎች መድረክ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ Previous Article ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከበረ Next Article ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ ተካሂዷል Print 1034