ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን በተመለከተ ለተከላካይ ጠበቆች ለሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን በተመለከተ ለተከላካይ ጠበቆች ለሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጠ

በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ከህዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የቆየ ተከታታይ ስልጠና ለተከላካይ ጠበቆች ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው ለህጻናት ምቹ እና ተስማሚ የሆነ የፍትህ ስርአት ግንባታን መሰረት ያደረገ ሲሆን ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰሎሞን ህጻናትን በሚመለከቱ ጉዳዩች ላይ ተመድበው የሚሰሩ ተከላካይ ጠበቆች ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን መገንባት ትውልድን ብሎም ሃገርን በዘላቂነት ከመገንባት ጋር የሚስተካከል ውጤት ያለው መሆኑን ተገንዝበው በስራቸው ለህጻናት መብት የሚጠነቀቅ የአሰራር ሂደትን፣ ለህጻናት ምቹ የሆነ ተግባቦትን እና በወንጀል ጉደይ ውስጥ ገብተው የሚገኙ ሃጻናትን የሚመለከቱ ህጎችን መርህ አድርገው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የስራ ላይ ስልጠናው የተሰጠው በዘርፉ በተግባር የዳበረ ልምድ እና እውቀት ባላቸው እንዲሁም ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን በተመለከተ የስልጠና ሞጁል በጋራ ባዘጋጁት የተከበሩ አቶ ደሳ ቡልቻ፣ ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ እና ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ሲሆን በስልጠናውም የህጻናትን እድገት እውደት እና እንደየ እድሜያቸው የሚኖራቸውን ስነልቦና መረዳት፣ ጥቃትን ለተቋቋሙ ህጻናት ምቹ የሆነ የአሰራር ሂደት አተገባበር / survivor centered approach /፣ ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአት መሰረታዊ መርሆች እና አተገባበራቸው፣ በወንጀል ጉዳይ ውስጥ ገብተው የሚገኙ ህጻናትን የተመለከከቱ ህጎች እና አተገባበራቸው የተዳሰሱ ሲሆን ተሳታፊዎችም በተግባር ከሚገጥሙ ችግሮችን እና ተሞክሮዎችን በማንሳት በውይይት ሃሳቦቹን አዳብረዋል፡፡

በመጨረሻም በስልጠናው መዝጊያ ላይ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ክብርት ዳኛ ህውስት አሸናፊ በሰጡት ማጠቃለያ ሰልጣኞች በሁለቱ ቀናት ቆይታቸው ያካበቷቸውን እውቀቶች በእለት ተእለት ስራቸው በመተግበር በወንጀል ጉዳይ ውስጥ ገብተው ለሚገኙ ህጻናት የሚሰጠውን የህግ ውክልና ከማሻሻል አንጻር፣ ወጥ የሆነ ለህጻናት መብት የሚጠነቀቅ አሰራር ሂደትን ከመተግበር እንዲሁም ሃላፊነት እና ርህራሄ የተሞላበት ሙያዊ አገልግሎት መስጠትን ባህል በማድረግ ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን በመገንባት ሂደት ተጨባጭ እና ዘለቄታዊ ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Previous Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የፌደራል የህግና ፍትህ ኢኒስቲትዩት 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስናን ቀን አከበሩ
Next Article ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሬጅስትራሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል
Print
433