ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት የተካሄዱ የትንተና ጥናቶች ላይ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ተጨማሪ ግብአት ሰጡ
/ Categories: News

ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት የተካሄዱ የትንተና ጥናቶች ላይ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ተጨማሪ ግብአት ሰጡ

በአማካሪ ድርጅት የሚሰራውን ሶስተኛው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት ሂደትን እንዲከታተል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቋቋመው ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ አማካሪ ድርጅቱ ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት ባካሄዳቸው የትንተና ጥናቶች ላይ ተጨማሪ ግብዓት ሰጠ፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሶስተኛውን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስትራቴጂካዊ ዕቅድ (2014-2018ዓ.ም) እንዲያዘጋጅ የተቀጠረው አድቫንስድ አሶሺየትስ እና አፕፍሮንት ጥምር አማካሪ ድርጅት ለስትራቴኪካዊ ዕቅድ ዝግጅቱ መነሻ እንዲሆኑ በሰሯቸው የትንተና ጥናቶች ላይ የሚመክር አውደ ጥናት ሚያዚያ 28 እና 29 ቀን 2013 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ የፌዴራል ፍርደ ቤቶች አፈጻጸም እና ተቋማዊ አቅም ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ባለድርሻ አካላት ትንተና ጥናት፤ እና ፖኢማቴከህ (PESTEL) ተጽዕኖዎች ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች አንጻር ትንትና ሪፖርት ለውይይት ቀርበዋል፡፡

የስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ትኩረት ሊሰጥባቸውና ሊመልሳቸው የሚገቡ አግባብነት ያላቸው ቁልፍ የሆኑ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን መለየት ዋንኛ ዓላማ የሆነው የፌዴራል ፍርደ ቤቶች አፈጻጸም እና ተቋማዊ ዓቅም ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት ሁለት ከፍሎች ያሉት ሲሆን በሰባት ምሰሶዎች/ Pillars/ ስር ጥልቅ ትንተና የቀረበበት ነው፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት፤ የዳኝነት/የፍርድ ቤቶች አገልግሎት ተደራሽነት፤ የፍርድ ቤት የችሎትና የፍርድ ሂደቶች፤ እና የህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የተዳሰሱ ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራርና አስተዳደር፤ የዕቅድ ሥርዓት፣ ፖሊሲዎችና መዋቅሮች እንዲሁም የሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ተቃኝነተዋል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ባለድርሻ አካላት ትንተና በፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ የስራ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ያላቸውን ባለድርሻ አካላት ውስጣዊና ውጫዊ በማለት በሁለት ከፍሎ ትንተናውን አካሂዷል፡፡ እንደ ባለድርሻ አካላት ትንተና ሪፖርት በዳኝነት ስራና ተቋም ውስጥ የሚሳተፉ የፍርድ ቤት የበላይ አመራር አካላት፤ ዳኞች፣ ሌሎች የጉባዔ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች የወስጥ ባለድርሻ ሲሆኑ ተገልጋይ ህብረተሰብ /ከሳሽና ተከሻስ/፤ ሁለቱ የፌዴራል ምክር ቤቶች፤ የፌዴራል መንግስት ተቋማት፤ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች፤ የፍትህና የህግ ጥናት ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ የሰብዓዊ መብት ጠባቂዎች፤ የክልል ፍርድ ቤቶች እና ማረሚያ ቤቶች የውጭ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ የትንተና ጥናቱ ባለድርሻ አካላቱ ከፍርድ ቤት የሚጠብቁትን፤ የሚጠብቁት ባይከናወን የሚያስከትለው ተጽዕኖ፤ ለተነሱ ጉዳዮች የአስፈላጊነት ደረጃ (Priority) እንዲሁም የፍርድ ቤቱ ተግባራዊ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ያመላከተ ሰነድ ነው፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው የትንተና ጥናት ፖኢማቴከህ (PESTEL) ተጽዕኖዎች ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች አንጻር ሲሆን በፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥና ሁለንተናዊ ቁመና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ፣ ከባቢያዊ እና የህግ ድባቦች ምልከታ ተደርጎባቸዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ በኩል የዓብይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በቀረቡት የትንተና ሪፖርቶች ወሰን፤ ጥልቀት እና ጥራት ላይ ያስተዋሉተን ጠንካራ ጎኖች አድንቀው ያስተዋሉትን አንኳር ክፍተቶች ለይቶ በማሳየት አማካሪ ድርጅቱ እንደገና እንዲያጤናቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በትንተና ጥናቶቹ ሽፋን ያላገኙ ጉዳዮችንም ጠቁመው የጥናቶቹ የመጨረሻ ሰነድ ላይ እንዲካተቱ ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም አማካሪ ድርጅቱ ከትንተና ጥናቶቹ በመነሳት ወደፊት ሰፊ ጥናትና ውይይት የሚደረግባቸው ነገር ግን አሁን ላይ መነሻ ውይይት እንዲካሄድባቸው አማራጭ ራዕይ፤ ተልዕኮ እና እሴቶች እንዲሁም ቁልፍ የትኩረት መስኮችን አቅርቦ በጉባዔው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ መዝጊያ ላይ ለአማካሪ ድርጅቱ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት እና የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት ዓብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር አቶ ተኽሊት ይመስል የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችን አመስግነዋል፡፡ ለዕቅድ ዝግጅቱ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ተግባራት የተከናወኑና ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅዱን ማዘጋጀት ቀጣይ ተግባር መሆኑን ገልጸው የዕቅዱ ትግበራ በመጪው ሐምሌ ይጀምራል ብለዋል፡፡ ለዚህም በቀሩት ሁለት ወራት በጋራ ስምምነቱ ላይ በተቀመጠው የተግባር የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስራውን ለማጠናቀቅ አማካሪ ድርጅቱ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበው በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድን ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ለዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች፤ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የበላይ አመራሮች፤ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም፤ ለዳይሬክተሮችና ዳኞች፤ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ከሁሉም ፍ/ቤቶች ለተወከሉ ባለሙያዎች እና ለባለድርሻ አካላት በተለያየ መድረክ ለውይይት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቶች በዘጠኝ ወሩ ከአንድ መቶ 19 ሺህ በላይ ለሆኑ መዛግብት እልባት ሰጡ
Next Article የተማሪዎችን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
Print
321