ለቀድሞዎቹ የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት አሸኛኘት ተደረገ
Temesgen Alemayehu
/ Categories: News

ለቀድሞዎቹ የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት አሸኛኘት ተደረገ

ለቀድሞዎቹ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት ለክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊና ለክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡

አሸኛኘቱን ያደረጉት አዲስ የተሾሙት የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንትነት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እና ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና የሶስቱም የፌደራል ፍ/ቤቶች አመራሮች ናቸው፡፡

በአሸኛኘት ሥነሥርዓቱ ላይ የቀድሞዎቹ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊና ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት ተሹመው ቃለ-መሀላ ከፈጸሙበት ከጥቅምት 22 ቀን 2011ዓ .ም ጀምሮ በኃላፊነት ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሕዝብ አመኔታ ያተረፉ የዳኝነት ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ ያከናወኗቸው የሪፎርም ሥራዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንትና የፌደራል ፍ/ቤቶች ቃል-አቀባይ በሆኑት በክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በእነርሱ አመራርነት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የፍርድ ቤቶች እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መውጣታቸው፣ የፍ/ቤቱ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀጥታ ተልኮ እንዲፀድቅ መደረጉ፣ የፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ከ16 በላይ ደንቦችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው እንዲፀድቁ መደረጉ፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸው፣ በዳኝነት አካሉ ውስጥ የጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ሥራዎች እና ሌሎችም የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም ተገልጋዩ ሕብረተሰብ አሁንም በዳኝነት አካሉ ላይ የሚያነሳቸው የአገልግሎት ጥራት፣ የተጠያቂነት፣ የሥነምግባር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም የፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች የመዋቅርና የስራ አካባቢን የማሻሻል ጥያቄዎችን የመመለስ ኃላፊነት ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ክቡር አቶ ተስፋዬ አንስተዋል፡፡

ክቡር አቶ ተስፋዬ የቀድሞዎቹ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት በቀጣይ የህይወት ጎዞአቸው ሁሉ መልካምነት፣ በጎነት እና ስኬት እንዲያጋጥማቸው በፍ/ቤቱ ማሕበረሰብ ስም ተመኝተውላቸዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ መንክር በበኩላቸው የፍ/ቤቱን ዳኞች በመወከል ባደረጉት ንግግር የቀድሞዎቹ የፍ/ቤቱፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት በኃላፊነት በቆዩበት ጊዜ የዳኝነት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና የፍ/ቤቱን የሕዝብ አመኔታ ለማሳደግ ያከናወኗቸውን ተግባራት በመግለጽ ላከናወኑት ሥራ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በክቡራን ዳኞች እና በፍርድ ቤቱ ማሕበረሰብ የተዘጋጀ የማስታወሻ ስጦታም የተበረከተላቸው ሲሆን የቀድሞዎቹ የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት በየበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በፍ/ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የዳኝነት አገልግሎቱን ለማሻሻል ከፍርድ ቤቱ ማሕበረሰብ ጋር ያደረጉትን ጥረት በመግለጽ ለአዲሶቹ የፍ/ቤቱ ተሿሚ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት እንዲሁም ለፍ/ቤቱ ማሕበረሰብ ቀጣዩ ጊዜ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው በመመኘት ለተደረገላቸው የአሸኛኘት ፕሮግራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች በስድስት ወራት ለ84,359 መዛግብት ዕልባት መስጠታቸው ተገለጸ
Next Article በፍርድ ቤቶች መልስ ሰጪን ሳያስቀርቡ ይግባኝን መዝጋት ወይም «አያስቀርብም» በማለት የሚዘጉ መዝገቦችን በተመለከተ የተካሔደ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደረገበት
Print
2541

Gallery