Thursday, September 17, 2020 / Categories: News ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ተመለከተ የንብረት ባለቤትነት ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ውጤታማ የሆነ የውል አፈጻጸም ሥርዓት በመዘርጋት ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ለመፍጠር እንዲቻል በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው በኩባንያ እና ኪሳራ ሕግጋት (Company and Insolvency Law) ዙሪያ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚሰሩ ዳኞች የተዘጋጀ የአራት ቀን ሥልጠና መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በአያት ሪጀንሲ ሆቴል ሲጀመር የፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ በሥልጠናው ላይ በፌደራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በንግድ እና ተያያዥ ችሎቶች ላይ የሚሰሩ 50 ዳኞች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በንግግራቸው በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የታቀደ መሆኑን በመጥቀስ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ዳኞች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ሥልጠናዎች ማዘጋጀት አንዱ መሆኑንና የአሁኑ ሥልጠናም የዚህ ዕቅድ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሀገራችን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ስራን ቀለል ለማድረግ (Ease of Doing Business) በተለያዩ አካላት ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች በጥብቅ ዲሲፒሊን እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በዳኝነት ዘርፉ እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም ሥራ ተፈጻሚ ለማድረግ በዕቅድ ከተያዙ ሥራዎች መካከል በንግድ ሕጉ ከተካተቱ ጉዳዮች በተጨማሪ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮችን የመለየት (Case Categorization) ሥራን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገኝበትም ጠቅሰዋል፡፡ የንግድ ችሎቶችን እንደገና የማደራጀት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በተለየ ሁኔታ የሚቋቋም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፍርድ ቤት የሚደራጅበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲሁም በእነዚህ ፍርድ ቤቶች በችሎቶች ላይ የሚመደቡ ዳኞች ችሎታ እና ብቃትን መነሻ በማድረግ የመመደቢያ መስፈርት (Guideline) ማዘጋጀት የበጀት ዓመቱ የሪፎርም ሥራ አካል እንደሆንም ተናግረዋል፡፡ በሥልጠናው ላይ በፌደራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በንግድ እና ተያያዥ ችሎቶች ላይ የሚሰሩ 50 ዳኞች በመሳተፍ ይገኛሉ፡፡ ሥልጠናው የሚያተኩርባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች የንግድ ማሕበራትን በተመለከቱ የንግድ ሕግ ድንጋጌዎች እና የኪሳራ ጉዳዮችን በሚመለከቱ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች እንዲሁም በተያያዥ ርዕሶች ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከመስከረም 6 – 9 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆየው የዚህ ስልጠና ዓላማ ዳኞች በንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በዚህ ረገድ የሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎቶችን ውጤታማ፣ ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ እንዲሁም ተገማች፣ ተጠያቂነት ያለበት እና የሕዝብ አመኔታን ያረጋገጠ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት ደ/ር ታደሰ ሌንጮ እና አቶ ስዩም ዮሐንስ ሲሆኑ አሠልጣኞቹ የንግድ ሕግ ረቂቅ በማዘጋጀት፣ በዩኒቨርሲቲ ንግድ ሕግ በማስተማር እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በአገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ጆርናሎች ላይ በማሳተም ዕውቅና ያላቸው ናቸው፡፡ ሥልጠናው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ተጠሪነቱ ለዓለም ባንክ በሆነው አይ.ኤፍ.ሲ (International Financial Corporation) ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የሥልጠናው ሒደት በአሰልጣኞች ከሚደረግ ገለጻ በተጨማሪ የዳኞችን የቡድን ውይይት እንደሚያካትት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Next Article የዳኝነትና የዳኞች ነጻነት መከበር ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ቁልፍ ማዕዘን ነው Print 1386