Wednesday, July 30, 2025 / Categories: News ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ጽ/ቤት የሰበር ውሳኔዎች የድምጽ ቅጂ ተበረከተ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሕትመት ተዘጋጅተው ከቅጽ 19-26 የወጡ የሰበር ውሳኔዎችን በድምጽ ቅጂ እንዲዘጋጁ በማድረግ ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ጽ/ቤት ሐምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም አበረከተ፡፡ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስብሰባ አዳራሽ በተካሔደ የርክክብ ሥነሥርዓት በሀርድ ዲስክ የተዘጋጀውን የድምጽ ቅጅ ለብሔራዊ ማሕበሩ ያስረከቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ሲሆኑ ማሕበሩን በመወከል ደግሞ የድምጽ ቅጅውን የተረከቡት የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ፕሬዚደንትና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ረታ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ከቅጽ 1-18 በሕትመት የተዘጋጁ የሰበር ውሳኔዎችን በድምጽ ቅጂ አዘጋጅቶ ለብሔራዊ ማሕበሩ ተደራሽ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን አሁን የተደረገው ርክክብ ደግሞ በሕትመት መልክ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ የተደረጉ ቀሪ የሰበር ውሳኔዎችን የማሕበሩ አባላትና ሌሎች አይነስውራን ዜጎች በማሕበሩ በኩል እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠባቸውን የሰበር ውሳኔዎች በኤሌክትሮኒክ እና በሕትመት የማሰራጨት ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ገልጸው እስካሁን ድረስ በቅርቡ የወጣውን ቅጽ 27 ጨምሮ በአጠቃላይ 27 ቅጾች ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ መደረጋቸውን ገልጸው የውሳኔዎቹ ተደራሽነት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ማድረግ ስላለበት ባለፈው ዓመት ከቅጽ 1-18 በሕትመት የወጡ የሰበር ውሳኔዎችን በድምጽ በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ማስረከብ እንደተቻለ ገልጸው አሁንም ከቅጽ 19-26 በሕትመት የወጡ የሰበር ውሳኔዎችን ወደድምጽ ቅጂ በመቀየር ለማሕበሩ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ርክክብ የተፈጸመባቸው የድምጽ ቅጂዎች ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል እንዲያገኛቸው በሕትመትና በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚሰራጩ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም ግን በተለያየ ምክንያት ይህን ለማግኘት የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ በድምጽ በሀርድ ዲስክ ከተዘጋጀው በተጨማሪ በዩቲዩብ (Youtube) ቻናል ተጭኖ በድምጽ አማራጭ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ እንደተቻለና ይህን አማራጭ ለሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ መደረጉ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ፕሬዚደንትና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ረታ በበኩላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው ውሳኔ ሕግ ሆኖ በሌሎች አካላት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በሕግ የተደነገገ መሆኑን ጠቁመው ከሕግ መርሆዎች አንዱ "ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም" የሚለው መሆኑንና ሕጎችን ተደራሽ ማድረግ ሕግ በሚያወጣው አካል ላይ የተጣለ ኃላፊነት በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይህን በመረዳት የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ለአይነስውራን ዜጎች ከሕትመት በተጨማሪ በድምጽ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባውና የሚመሰገን እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ለፍርድ ቤቱ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ለሌሎችም አጋር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ በሰበር ውሳኔዎች የሚሰጡ የሕግ ትርጉሞች በቀጣይ ለሚሰጡ ውሳኔዎች አስገዳጅ ስለሚሆኑ የሕግ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል እነዚህን ውሳኔዎች የማወቅ መብት ያለው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ Previous Article የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭ ማዕከል የህንፃ እድሳት ምርቃት መርሃግብር ተካሄደ Next Article የሰበር ሰርዓትን ማጠናከር ለዳኝነት ሪፎርም በሚል የቀረበ ጽሁፍ ላይ ውይይት ተደረገ Print 646