ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ፣ረዳት ዳኞች እና ሬጂስትራሮች ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ፣ረዳት ዳኞች እና ሬጂስትራሮች ስልጠና ተሰጠ

ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቆች ፣ ረዳት ዳኞች እና ሬጂስትራሮች “ Work Related Stress Management” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ሐምሌ 9 እና 11 ቀን 2016 ዓ.ም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የስልጠናው ትኩረት የፍርድ ቤቱ ተከላካይ ጠበቆች ፣ረዳት ዳኞች እና ሬጂስትራሮች በተለይ ከዕለት ተዕለት ስራቸው ጋር በተያያዘ ጫናዎችን የሚያስተናግዱበት ፣የተፈጠሩትን ጫናዎችን ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበት ክህሎት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡

የስልጠናዉን መድረክ በንግግር የከፈቱት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን ስልጠናዉ በሥራ ጫና ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ የጤና መታወክ ለመገንዘብና ወቅታዊ ሳይንሳዊ መፍትሄ ለመስጠት እጅግ አጋዥ መሆኑን በማመልከት ስልጣኞች የሕዝብ አመኔታ ያተረፈ ተቋም በመገንባት ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደመሆናቸዉ በሥራ ጫና ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ጫናዎች ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸዉ በሥራቸዉ ይበልጥ ዉጤታማ መሆን እንዲችሉ ስልጠናዉ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቁመዋል።

በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ስልጠና የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክ መምህርት የሆኑት ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ሲሆኑ በገለጻቸው ወቅት የስራና ጫና የሚፈጠሩባቸውን ምክንያቶች ፣የሚያደርሰው የጉዳት መጠን ፣ በስራ ጫና ሳቢያ የሚፈጠሩ ባህሪያቶችና ምልክቶቻቸው እና ራስን ከውጥረት ለመከላከል መደረግ ስላለባቸው ተግባራት ላይ ሰፊ ገለጻና የተግባር ልምምድ ሰጥተዋል።

የስልጠናዉን መዝጊያ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ዙፋን ወ/ገብርኤል በበኩላቸው ይህ ስልጠና ቀጥታ ከህግ ስራ ጋር የሚገናኝ ባይሆንም ዘወትር ከእለት ተዕለት የሥራ ሕይወት ጋር ተያይዘው ሊፈጠሩ የሚችሉትን ውጥረቶች በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል የሚያግዝ በመሆኑ ሰልጣኞች ከስልጠናዉ የቀሰሙትን ዕዉቀትና ክህሎት በመጠቀም ለሙያዊ ሕይወታቸዉ ዉጤታማነት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአፍሪካ ህብረት በህጻናት ጥበቃ ጉዳዮች እና ሌሎች ጎጂ ተግባራት በኢትዮጵያ ሀገራዊ የክትትል ተልዕኮ ወርክሾፕ ላይ በመገኘት ሪፖርት አቀረበ
Next Article የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬደዋ ምድብ ችሎት የቢሮ እድሳት የምርቃት ስነ-ስርዓት ተካሄደ
Print
1744