ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተጠናቀቀ
/ Categories: News

ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተጠናቀቀ

በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተተገበሩ የሚገኙ የለውጥ ሥራዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲረዳ ከሶስቱም ደረጃ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ ዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ መካከለኛ አመራሮች እና ሌሎች ሰራተኞች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በስድስት ዙሮች በመስጠት ተጠናቀቀ፡፡

የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት የሕግ ማሻሻያዎች፣ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ለዉጥ፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እንዲሁም የሰው ኃይል የአቅም ግንባታ ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የለውጥ ሥራው የሚተገበረው በሰው ኃይል በመሆኑ በተከታታይ ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ዓላማ የፍርድ ቤቶችን የሰው ሀብት አቅም በመገንባት የሚተገበረውን የለውጥ ሥራ ተፈጻሚ ለማድረግ ብቃት፣ ዝግጁነት እና ተነሳሽነት እንዲኖረው ለማስቻል ነው፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎቹ በየዙሩ የተሰጡት ከፍርድ ቤቶቹ ባሉት አመራሮች እና ከዉጭ በተጋበዙ አሰልጣኝ ሲሆን የለዉጥ ስራዎች ትግበራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የተክኖሎጅ ለዉጦች እና አጠቃቀም፣ የሰራተኞች አስተዳደር መመሪያዎች እና አመራርነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸዉ፡፡

ስድስተኛዉ እና የመጨረሻዉ ዙር ላይ ለመካከለኛ አመራሮች ማለትም ለዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች እና በተመሳሳይ ደረጃ ላሉት አመራሮች ተቋማዊ መርሆዎች፣ የዘመናዊ ተቋማት መገለጫዎች፣ ተቋማዊ ለውጥ እና ባህል፣ ተቋማዊ አመለካከት (Organizantional Mindset) እና በአመራርነት ክህሎት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን የሰጡት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት እያገለገሉ ያሉ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች የሰው ኃብት ሥራ አመራር ጉባኤ አባል የሆኑት የተከበሩ ከበደ ገነቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በሥልጠናው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር በዚህ ስልጠና ተሳታፊ የሆኑ አመራሮች በተሰጣቸዉ ኃላፊነት እና ዉስጣቸዉ ባለዉ አቅም ልክ አዳዲስ አሰራሮችን እና የፈጠራ ክህሎት በመጠቀም የፌደራል ፍርድ ቤቶች በቀጣይ በሚኖሯቸዉ የለዉጥ ስራዎች ልክ ዝግጁ ሆነዉ ማገልገል፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት በመስራት ተቋማዊና ሀገራዊ ተልዕኮ ከመፈጸም አንጻር የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

Previous Article የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ
Next Article የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ክልላዊ ዳይሬክተር (The office of the United Nations High Commissioner for Human Rights (OHCHR) regional director) ሚስተር ማርሴል አክፖቮ የተመራ ልዑክ ቡድን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት
Print
865