ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮግራም ተጠናቀቀ
/ Categories: News

ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮግራም ተጠናቀቀ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የስራ ሃፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በሶስት ዙር ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ነሃሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ስልጠና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች፣ በሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም በሶስተኛው ዙር ስልጠና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

በስልጠና ፕሮግራሙ ላይ ሁለት የመወያያ ጽሑፎች በ ዶ/ር ደምመላሽ ሽፈራዉ እና ዶ/ር ታደሰ ስሜ የቀረቡ ሲሆን በተለይ ከወንጀል ተጠያቂነት እንጻር በሽግግር ፍትህ ፖሊሲዉ ዉስጥ የተካተቱት ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ እንዲሁም የወንጀል ፍትህ ስርዓቱ ጥራት ባለዉ መልኩ እንዴት ሊተገበር እንደሚገባ በስፋት ተነስቷል።

በሁለኛው ዙር ስልጠና የሽግግር ፍትህ ብሄራዊ የማማከር ሂደት ትግበራን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ በዶ/ር ታደሰ ካሳ እና አዲስ ጌትነት፣ ዳኞችን የተመለከቱና በሽግግር ፍትህ ሂደት ዘርፈ ብዙ ለዉጥ ሊያመጣ የሚችል ጥናታዊ ጽሁፍ በዶ/ር ታደሰ ስሜ የቀረበ ሲሆን በሶስተኛውና የመጨረሻው ዙር ስልጠና የሸግግር ፍትህ ሂደት በሃገር አቀፍ ደረጃ የማማከር ሂደት ምን እንደሚመስል በዶ/ር ታደሰ ካሳና አዲስ ጌትነት እንዲሁም ዳኞች በሽግግር ፍትህ ሂደት የሚጣልባቸዉን ሃላፊነትና ተጠያቂነትን አስመልክቶ በዶ/ር ታደሰ ስሜ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም “Work Related Stress Management” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የክህሎት ስልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክ መምህርት በሆኑት ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው አላማም ዳኞችና የፍርድ ቤት የስራ ሃላፊዎች ከስራ ጋር በተገናኘ ጫናዎችን የሚያስተናግዱበት፣ የሚቋቋሙበትንና የአመራር ክህሎትን የሚያሳድጉባቸው ዘዴዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨባጫ መስጠት ነው።

በቀረቡት ገለጻዎች ላይም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ከተሳታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የሽግግር ፍትህ ሂደት እና ትግበራ የወንጀል ፍትህን በማገዝ ረገድ ያለዉን ጠቀሜታ ገልጸዉ ዳኞች በሽግግር ፍትህ ሂደት ዙሪያ ከስልጠናው ያገኙትን እዉቀት በተግባር ላይ በማዋል እና ፍርድ ቤቶች ያለባቸዉን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት መስራት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡ ክብርት ምክትል ፕሬዚዳንቷ አክለዉም ከስልጠናው የተገኙ እዉቀትና ክህሎቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም እና በችግሮቹ ዙሪያ በተባበረ ክንድ ተረባርቦ በመስራት የፍርድ ቤቶችን የህዝብ አመኔታ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶች ከግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ታማኝነትና ገለልተኝነት አንጻር ምን መምሰል እንዳለባቸዉና የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በማብራራት ክቡራን ዳኞች የእረፍት ጊዜያቸዉን ሰዉተዉ በስልጠናው ላይ በመገኘታቸው አመስግነዋል፡፡

Previous Article ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ መግለጫ
Next Article የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ
Print
262