ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች "Building the power of trust and enhancing judicial integrity" እና "The role of technology in building judicial trust and enhancing accessibility" በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከቀን 01-02/02/2018 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የቆየ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የዳኝነት ስራ ከእውቀት እና ከክህሎት በተጨማሪ ከባህሪይ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ እና የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሀብት አዕምሮ እንደመሆኑ አዕምሮ ላይ ለመስራት መልካሙን በማየት፣ በማሳየትና የተሻለ በማሰብ በጥሩ መንፈስ ዓመቱን መጀመር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ዩዳሄ አርዐያስላሴ በበኩላቸው የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር የለማውና በመላው ሀገሪቱ ሊተገበር የሚችል የፍርድ ቤቶች የተቀናጀ የኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር (ICMIS) ሲስተም ተገልጋዮች ጉዳያቸውን በቀላሉ የሚያቀርቡበት፣ የሚከታተሉበት፣ የሚከራከሩበት፣ መረጃ የሚያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው የመዝገብ ክምችን ለመቀነስ እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልም ይረዳል ብለዋል፡፡ አክለውም የሀገራችንን ፍርድ ቤቶች አሰራር ከወረቀት ወደ ኤሌክትሮኒክ ለመቀየር ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ይህን ቁልፍ ሂደት አልፎ ወደ መሬት ማውረድና ዜጎች እንዲገለገሉበት ማድረግ ትልቅ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመጀመሪያዉ የፍ/ቤቶች አመኔታን የሚመለከት ስልጠና የሰጡት ዶ/ር ምህረት ደበበ ሲሆኑ የተቀናጀ ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር (ICMIS) ሲስተም ላይ ስልጠናዉን በመስጠት የተሳተፉ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች አቶ ብዙነህ በቀለ እና አቶ አቤኔዘር ግርማንዴ ናቸው፡፡

በቀረቡ ገለጻዎች ላይ በርካታ ጥያቄዎች እና ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ፍርድ ቤቶች በሪፎርም ስራ ላይ መቆየታቸውን ጠቅሰው የለሙት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ተጨባጭ እንዲሆኑ ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ የዳኞች ሚና ወሳኝ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የተሰጡት ስልጠናዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሄደ
Next Article 18ኛው የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከበረ
Print
371