ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሬጅስትራሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል
/ Categories: News

ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሬጅስትራሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል

ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሬጅስትራሮች ለሬጅስትራሮች በተዘጋጀ የሥልጠና ሞጁልና ሞጁሉ ከተዘጋጀ በኋላ በወጡ ሕጎች እና በአሰራር የሚታዩ ክፍተቶችንን መሰረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ስልጠናው በዋነኛነት የሬጅስትራር ተግባርና ሀላፊነት፤ የሥነ-ስርዓት ህጎች ከማሳካት አኳያ ሬጅስትራሮች ያላቸው ሚና፤ በፍርድ አገልግሎት የውክል ህግ እና በአተገባባር ላይ ያሉ ክፍተቶች፣ በአዲሱ የዳኝነት ክፍያ ደንብ የዳኝንት አከፋፈል ስርዓት እና ለሬጅስትራር የተሰጠ ሀላፊነት፣ የሬጅስትራር አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፤ በሬጅስትራር አገልግሎት ላይ በአሰራር የሚታዩ ክፍተቶችና መፍትሄዎቻቸው እና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በዕቅድ ከተያዘው ዋነኛው ተግባር የባለሙያውን አቅም ማሳደግ እንደሆነ ገልጸው በሬጅስትራር ረገድ ጥናት በማድረግ የስልጠና ሞጅሎችን በማዘጋጀት እየተተገበረ አንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ከችሎት በመለስ የሬጅስትራር ክፍል ለዳኝነት አካሉ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ገልጸው በተለይ ስልጠናው የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በተቀላጠፈ መንገድ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑን ሰልጣኞች በክህሎት የተሻሉ እንዲሆኑ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ዙፋን ወ/ገብርኤል በበኩላቸው የስልጠናው አላማ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከዚህ ቀደም በተበታተነ መልኩ ይሰጡ የነበሩ ስልጠናዎችን ወደ አንድ በማምጣት፣ ጥናት በማስጠናት፣ ክፍተቶችን በመለየትና ሞጁሎችን በማዘጋጀት ወጥነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለመስጠት፤ በተጨማሪ ሞጁሉ ከወጣ በኋላ የወጡ ህጎችና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመለየት ስልጠናው የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ስለልጠናው የሬጅስትራሮችን አቅም ከመገንባት በተጨማሪ ወጥነት የሌላቸው አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶችን ወጥ እንዲሆን በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል ፡፡

ስልጠናው የተዘጋጀው በፌደራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ሲሆን በ4 ዙር የሚሰጥ ሆኖ ለመጀመሪያው ዙር ሰልጣኞች ከታህሳስ 03-04 ቀን 2018 ዓ.ም ስልጠናውን በሚሰጡት አሰልጣኞች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ዙፋን ወ/ገብርኤል ፤በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ህይወት ማሙሸት እና በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ፈትለወርቅ አንዳርጌ እየተሰጠ ይገኛል ፡፡

Previous Article ለህጻናት ተስማሚ የፍትህ ስርአትን በተመለከተ ለተከላካይ ጠበቆች ለሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጠ
Next Article ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት አባል የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ
Print
222