ለፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ሠራተኞች በንቃተ-ሕግ እንዲሁም ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሥነልቦናዊና በማሕበራዊ ድጋፎች እና መርሆዎች ላይ ሥልጠና ተሰጠ
ለፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ሠራተኞች በንቃተ-ሕግ እንዲሁም ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሥነልቦናዊና በማሕበራዊ ድጋፎች እና መርሆዎች ላይ ሥልጠና ተሰጠ
*****************************************************************
ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ ሬጅስትራሮችና የአስተዳደር ሠራተኞች በንቃተ ሕግና የሴቶች ሰብዓዊ መብቶች በዓለም አቀፍና በኢትየጵያ ሕግ ላይ እንዲሁም ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሥነልቦናዊና ማሕበራዊ ድጋፎችና መርሆዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
ሥልጠናው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግና አስተዳደር ኮሌጅ ጋር በመተባበር በተከታታይ የሚካሄዱ ሥልጠናዎች አካል ሲሆን በአዳማ ከተማ በሚገኘው ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለሁለተኛ ዙር ከታህሳስ 18 _ 19 ቀን 2015 ዓ᎐ም ሲካሄድ 150 ያህል ሠልጣኞች ተሳትፈውበታል፡፡
ለፍርድ ቤቱ ሬጅስትራሮችና የአስተዳደር ሠራተኞች የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ከሕዳር 22 _ 25 ቀን 2015 ዓ᎐ም የተሰጠ ሲሆን የአሁኑ ዙር ሥልጠና ደግሞ ቀደም ሲል በተካሔደው ሥልጠና ላይ ዕድሉ ላልደረሳቸው ሠራተኞች የተዘጋጀ ነው፡፡
በንቃተ_ ሕግ ላይ ያተኮረው ሥልጠና በሕግ ጽንሰ ሐሳብ ምንነት እና ዓላማ፣ በዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሕጎች፣ በዋና ሕጎች እና የሥነሥርዓት ሕጎች፣ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በዓለም አቀፍ ሕጎች እና በአገራችን ሕጎች ስላላቸው ቦታ እንዲሁም የሴቶች ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ለማድረግ በኢ᎐ፌ᎐ዲ᎐ሪ ሕገመንግሥት እና በሌሎች የአገራችን ሕጎች ያሉ ድንጋጌዎችን የተመለከተ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ ሊደረጉ ስለሚገቡ ሥነልቦናዊና ማሕበራዊ ድጋፎችና መርሆዎችን በተመለከተ በተሰጠው ሥልጠና ጾታዊ ጥቃት ስለሚያደርሰው ስነልቦናዊ ጫና እና ማሕበራዊ መዛባት፣ ለተጠቂዎቹ እገዛ ለማድረግ ሊተገበሩ ስለሚገባቸው መርሆዎች፣ ሥነልቦናዊ እና ማሕበራዊ ደህንነትን ለመጠበቅ አስፈላጊ በሆኑ የተግባቦትና የሙያ ክህሎቶች እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትምህርታዊ ማብራሪያ ቀርቦ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጎበታል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ሥልጠናው ከፍተኛ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸው በአገራችን በሴቶች ላይ የሚታየውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስተያየት አቅርበዋል፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
293