Monday, May 13, 2024 / Categories: News ለ45 ተከላካይ ጠበቆች 2ኛ ዙር የ6 ቀን አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት እና በፌዴራል የሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ትብብር በተመረጡ በፀረ-ሽብር አዋጅ ፣ በተከላካይ ጠበቃ ሙያ ስነምግባር እና በተመረጡ የወንጀል ገዳዮች ከግንቦት 5 - 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የ6 ቀናት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናዉ 45 ተከላካይ ጠበቆች የሚሳተፉ ሲሆን በእያንዳንዳቸው የስልጠና ርዕሶች ሰፊ ልምድ ያላቸዉ 3 አሰልጣኞች ስልጠናዉን የሚሰጡ ይሆናል። ስልጠናው የሰልጣኞችን እዉቀትና ክህሎት ለማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ ያለዉ ሲሆን የሚያገለግሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች በብቃት ፣ በትጋት ፣ በጥራት እና በተጠያቂነት ስሜት እንዲያገለግሉ አመለካከቻቸዉን ጭምር ያግዛቸዋል ተብሎ የታመነበት ስልጠና ነዉ። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ድምፅ ለሌላቸዉ ድምፅ ፣ ገንዘብ ለሌላቸው ገንዘብ እና በፍትህ ስርዓቱ ዉስጥ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መከታ በመሆን በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተከላካይ ጠበቆች ሥራቸውን በኃላፊነት ስሜት ፣ በቅንነት ፣ በስነምግባር እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጠናዎችን በሞጁል ከማድረግ በተጨማሪ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ e-learning መርሐግብር ለመጀመር እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ይህ ስልጠና መሰጠቱ ትልቅ አዎንታዊ ፋይዳ ያለዉ መሆኑን አክለው ስልጠናዉ ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ሰልጣኞች በንቃት በመሳተፍ የስልጠናው ዓላማ እንዲሳካ የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ከበደ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ለተገልጋይ በተለይም አቅም ለሌላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመንግስት ወጪ ሙያዉ በሚጠይቀዉ ስነምግባርና ትጋት የተሟላ ተከላካይ ጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ስልጠናዉ መሠረት የሚጥል መሆኑን አመልክተዋል። በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተከላካይ ጠበቆች የሚጫወቱት የማይተካ ሚና በፍርድ ቤትና በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዲያድግ ትልቅ ድርሻ ያለዉ መሆኑን ተገንዝበዉ ሰልጣኞች ስልጠናውን በጥብቅ ዲስፕሊን በንቃት እንዲሳተፉ አፅንኦት ሰጥተዋል ። በተመሳሳይ ርዕሶች የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ለ45 ተከላካይ ጠበቆች ከሚያዝያ 14 - 19 ቀን 2016 ዓ.ም ለ6 ቀናት የተሰጠ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በ2ኛ ዙር የስልጠና መርሐግብር በመጀመሪያ ዙር ስልጠና ያልተሳተፉ ሰልጣኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ። Previous Article የህጻናት ተስማሚ ፍትህ ሞጁል ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ Next Article በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር እና የዳኝነት ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም የአውሮፖ ህብረት ወንጀል ፍትህ አስተዳደር ማሻሻያ ፕሮጀክት አመታዊ ሪፖረት ላይ ከግንቦት 9 ቀን እስከ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት ተካሔደ Print 413