Tuesday, May 24, 2022 / Categories: News ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሕጋዊነቱ ባልተረጋገጠ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙት ኮሎኔል ገሙቹ አያና ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከቀረበባቸው ክስ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በነጻ ከተሰናበቱ በኋላ ህጋዊነቱ ባልተረጋገጠ ሁኔታ የተያዙና ይህ ውሳኔ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በእስር ላይ የሚገኙትን ኮሎኔል ገመቹ አያና ከእስር እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡ ለፌዴራል ፖሊስም ተጠርጣሪውን በዛሬዋ ዕለት እንዲለቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመልካችነት በመዝገብ ቁጥር 222914 የቀረበለትን መዝገብ መርምሮ የተጠርጣሪውን (የኮሎኔል ገመቹ አያና) አያያዝ እና እስር ሕጋዊነትን በተመለከተ የማስረዳት ሀላፊነት ያለባቸው የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የአያያዛቸውን ሕጋዊነት ያላስረዱ በመሆኑ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እና ነጻነቶች የማስከበር ተፈጥሮአዊ ሥልጣን ያላቸው እና ሕገመንግስታዊ ግዴታቸውም ጭምር ነው ያለው ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህ ሕገመንግስታዊ ግዴታም መብቱ ተጥሶብኛል የሚለው ወገን ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት ወይም ፍርድ ቤቱ መብቱ የተጣሰ ስለመሆኑ በየትኛውም ደረጃ ላይ ባለ ክርክር ራሱ ሲደርስበት በላቀ ሁኔታ ሊተገበር የሚገባ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሕግ አስፈጻሚ የሆኑት ፖሊስ እና ዓቃቤሕግም ሰብአዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን የማስከበር ሕገመንግስታዊ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት መብቱን ለማስከበር ሊተጉ እና ሊያስፈጽሙ ይገባል ሲል ችሎቱ ውሳኔ በሰጠበት ሃተታው አጽነኦት ሰጥቷል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠውን ውሳኔ ከታች ያለውን መስፈንጠሪያ በመጫን ከፍርድ ቤቱ ድረ-ገጽ ማግኘት ይችላሉ፡፡ https://www.fsc.gov.et/Digital-Law-Library/Judgments/Cassation-Decisions/%e1%8a%a5%e1%8a%90-%e1%8a%ae%e1%88%8e%e1%8a%94%e1%88%8d-%e1%8c%88%e1%88%98%e1%89%b9-%e1%8a%a0%e1%8b%ab%e1%8a%93-%e1%88%ae%e1%88%ae-%e1%8a%a5%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%8d%8c%e1%8b%b4%e1%88%ab%e1%88%8d-%e1%8c%a0%e1%89%85%e1%88%8b%e1%8b%ad-%e1%8a%a0%e1%89%83%e1%89%a4-%e1%88%85%e1%8c%8d-%e1%8b%a8%e1%88%b0%e1%88%98%e1%89%81-222914 የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-ሰነድ አስተዳደር ስርዓት (e-RMS) ልማትና ትግበራ ጽንሰ-ተልዕኮ (Inception Mission) መርሃ ግብር ተካሄደ Next Article በአስተዳደር ዘርፍ የፍርድ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሰራተኞውን የመፈጸም ዓቅም ለማጎልበት የሰራ መሆኑ ተገለጸ Print 2040 Documents to download የሰ.መ.ቁ 222914(.pdf, 669.41 KB) - 487 download(s)