Tuesday, April 8, 2025 / Categories: News ሰባተኛ ዙር የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ ተካሔደ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ ምክትል ፕሬዝደንቶች፣የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች፣ የፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተወካይ ዳኞች፣ የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንቶች፣የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶችን በአባልነት ያቀፈው ሰባተኛ ዙር የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ጉባኤውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በንግግር ያስጀመሩ ሲሆን ጉባኤው በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2017 ዕውቅና ተሰጥቶት የሚካሔድ መሆኑን ጠቅሰው በፍትሕ አስተዳደር ረገድ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አሰራር ሊያሻሽሉ የሚችሉ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ የሕግ ማውጣት ወይም ማሻሻል ሀሳብ ማመንጨት፣ የዳኝነት ሥራን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን ዋና ዋና ኃላፊነቶች እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ ጉባዔው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት አንጻር እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት በቂ ባለመሆናቸው ትኩረት እንዲሰጠውና የጉባኤውን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ አቅጣጫ በጉባኤው መቀመጥ እንዳለበት ክቡር ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በሆኑት በክቡር ዳኛ ቀነዓ ቂጣታ "በፌደራል ሥርዓት ውስጥ የሰበር ችሎት ሚና እና አተገባበር" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን ይህን ተከትሎም የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ዳኛ ፊጣ ደቻሳ "የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ከክልል ፍርድ ቤቶች እይታ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሑፍ ቀርቦ በተሳታፊዎቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በሰበር ከሚሰጡ ውሳኔዎች አስገዳጅነት ጋር በተያያዘ በፌደራል እና በክልል ያለው እይታ በውይይ የተቃኘባቸው ጉዳዮች ሲሆን ክልሎች በፌደራሉ ሥርዓት ትይዩ የሕግ ተርጓሚ አካላት ያደራጁ ቢሆንም በፌደራል ደረጃ የተዘረጋው የሰበር ሥርዓት ሁለቱን የዳኝነት አካላት የሚያገናኝ በመሆኑ በዚህ የጋራ አጀንዳ ላይ ጉባኤው መምከሩ ተገቢ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ Previous Article በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ የጋራ አቋም በመያዝ ተጠናቋል። Next Article የUNODC (United Office on Drugs and crime) የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስ አሺታ ሚታል ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጋር ውይይት አደረጉ Print 234