Friday, February 14, 2025 / Categories: News "ስነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች "ስነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ከፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ ከፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ፅ/ቤት እንዲሁም ከፌደራል ፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎችና ሬጅስትራሮች የተሳተፉበት የሁለት ቀናት ስልጠና የካቲት 5 እና 6 2017 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በመክፈቻ ንግግራቸው ሀገር ከሙስና የፀዳች እንድትሆን ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ሙስናና ብልሹ አሰራር አሁንም በየተቋማቱ ያልተቀረፈ ችግር መሆኑን አመልክተዉ መልካም ስነ ምግባር ያለው አመራር በስሩ ያሉትን ሰራተኞች በዛው ልክ የማብቃትና ጥሩ ተምሳሌት መሆን የሚችል በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ስልጠናዎች እና ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ለአመራሮችና የስራ ሃላፊዎች መስጠት ሙስናን ለመከላከል፣ መሰረታዊ የባህሪ ለዉጥ ለማምጣት እንዲሁም መልካም ዜጋን ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ከፍል መምህር እና የማህበራዊ ሳይንስ ፋካሊቲ ዲን የሆኑት ዶ/ር ታዬ ደምሴ ስልጠናው ከግንዛቤ ባሻገር ስር ነቀል የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የታለመ መሆኑን አንስተው የሙስናን ተለዋዋጭ ባህሪያትን በመረዳት ተገቢውን የመከላከያ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ፣ የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት ማዕቀፍ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀው ይህም ስልጠና የዚህ እርምጃ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በመቀጠልም በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይነስና አለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ከፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ታዴ ደጌ የሙስና ተጋላጭነትና መከላከያ ስልቶች ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በተመለከተ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው በፍርድ ቤቶች የሚታዩ የሙስና አሰራሮችን ለመለየት የስራው አካላትን ማወያየት አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች ለሙስና ያላችውን ተጋላጭነት በተመለከተም የዳሰሳ ጥናትን መሰረት በማድረግ የስራ ክፍሎች ከሚሰጡት አገልግሎቶች አንፃር ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡ አያይዘውም በፍርድ ቤቶች ለሚስተዋሉ የሙስና አሰራሮች ገፊ ምክንያቶች፣ አደጋዎችና ቁልፍ የመከላከያ ስልቶችን ብሎም የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ከሀገራችን ሁነት ጋር በንፅፅር መልክ በዝርዝር አንስተዋል፡፡ በፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና መረጃ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን በላይነህ በበኩላቸው ሙስናን ለመከላከልና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ አሰራርን መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸው በስልጠናው ማጠቃለያ አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ መሰል የስነ-ምግባር የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት እና የአሰራር ስርአት በመዘርጋት የተጠያቂነት እንቅስቃሴን ማስፈን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ ስልጠናው በነባራዊ እውነታ እና የዕለት ከዕለት የፍርድ ቤቶች የስራ ክንውን ላይ በመመስረት የታዩ ብልሹ አሰራሮች እና ተያያዥ መፍትሄዎች በውይይት የዳበሩበት ነበር፡፡ Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ Next Article የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስትር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የስራ ጉብኝት አደረጉ Print 900