Monday, June 13, 2022 / Categories: News በሃገራችን የሰብዓዊ መብትን ለመጠበቅም ሆነ ለማስከበር በቂ የህግ ማዕቀፍ ያለ መሆኑ ተገለጸ “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች አተገባበር በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች” በሚል ርዕስ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የህግ ባለሙያዎች የአንድ ቀን ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የስልጠናው ዋና ዓላማ የህዝብ ጥቅም የሚነኩ ክርክሮች ጽንሰ ሃሳባዊ ማዕቀፎችን፣ በኢትዮጵያ ሃገራዊ የዳኝነት ስልጣን ወሰን የሰብዓዊ መብቶችን የተመለከቱ ክርክሮችን ለመዳኘት የሚያግዙ በስራ ላይ ያሉ የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም መሰረታዊ መብቶችንና ነጻነቶችን ለመተግበር የሚረዱ የህግ ማዕቀፎችን በስልጠናው ለተሳተፉ ዳኞችና ህግ ባለሙያዎች ማስገንዘብ እና የጋራ መረዳት መፍጠር ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በስልጠናው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ በፍርድ ቤቶች ዘወትር የሚነሳ መሆኑን ገልጸው ለዳኝነት በሚቀርቡ እያንዳንዳቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ የህግ ትርጓሜዎች የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች በህግ ትርጓሜያቸውና ዳኝነት አሰጣጣቸው በህገመንግስት በግልጽ የተደነገጉ የሰብአዊ መብቶችን መሰረት ማድረግ አለባቸው ያሉት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ሃገራችን የተቀበለቻቸውና ስምምነቷን የገለጸችባቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችንም የውሳኔያቸው አካል ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች ሰብዓዊ መብቶችን ከማስከበር አንጻር ያለባቸው ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት ም/ፕሬዝደንቱ ይህንኑ ሚናቸውን እንዲወጡ ዳኞች በተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ውስጥ የተካተቱ ድንጋጌዎችን ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ክቡር አቶ ሰሎሞን አረዳ ኢትዮጵያ ሃገራችን ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ከበቂ በላይ የህግ ማዕቀፎች ያሏት መሆኑን በንግግራቸው የገለጹ ሲሆን በተለይም በቅርቡ ጸድቆ በስራ ላይ በዋለው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 11(4) ማንኛዉም በጉዳዩ ላይ መብት ወይም ጥቅም ያለዉ ሰዉ ወይም ጉዳዩን ለማቅረብ በቂ ምክንያት ያለዉ ሰዉ መሰረታዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን ለማስከበር በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው መደንገጉ ቀደም ባሉት የህግ ማዕቀፎች የሰብዓዊ መብትን ከማስከበር አንጻር የነበሩ ክፍተቶችን ለማቀራረብ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በስልጠናው አራት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ገለጻዎች የተደረጉ ሲሆን የመጀመሪያው የህዝብን ጥቅም የሚነኩ ከርክሮች ጽንሰ ሃሳባዊ ማዕቀፎች (Strategic Litigation Theoretical and conceptual frameworks) ላይ ማዕከል አድርጎ የህግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ አምሃ መኮንን ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ ይንንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ሃገራዊ የዳኝነት ስልጣን ሰብዓዊ መብቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የህግ ማዕቀፎችን (Legal Frameworks for Human Rights Strategic Litigation in Ethiopia’s Domestic Jurisdictions) በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምጣኔ ሃብት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኒ አባተ ምልከታ የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም ዓለም አቀፋዊ እና አከባቢያዊ የሰብዓዊ መብቶች ሥርዓት መልካም ተሞክሮ (International and Regional Human Rights Systems: Practical Takeaways) የ Expedite Justice ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ሲንቲያ ታይ ሃሳብ አካፍለዋል፡፡ በመጨረሻም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ዳኛ ዶ/ር ተፈሪ ገብሩ በመሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ላይ የዳኝነት አተገባበር (Judicial Enforcement of Basic Rights and Freedoms) በሚል ርዕስ በተለይም የሰበር ውሳኔዎች ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር የነበራቸውን ይዘት የተመለከተ ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ በገለጻዎቹ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን እና ዕይታቸውን ያንጸባረቁባቸው ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ሰብዓዊ መብቶችን ከማስጠበቅ እና ከማረጋገጥ አንጻር ተመሳሳይ ስልጠናዎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሊሰጣቸውና በሃገራችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና አተገባበር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ በአስተያየቶቶቻቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ስልጠናው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ከፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡ የህግ በለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች በቅርቡ በህግ ባለሙያዎች የተቋቋ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶቸ እንዲረጋገጡ የህግ ማዕቀፍ ሊወጣላቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ረቂቅ ህጎችን በማዘጋጀት፣ ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት እንዲሁም ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተገናኙ ጥናቶችን በማከናወን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሆነ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መታሰቢያ ኃይሉ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article የፍርድ ቤቱን የአስተዳር ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሰጠው አንድም የዳኝነት ሹመት የለም Print 2169