በህፃናት የቀለብ አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ ዉይይት ተደረገ
/ Categories: News

በህፃናት የቀለብ አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ ዉይይት ተደረገ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ባዘጋጀዉ የህፃናት ቀለብ አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ ላይ የግብአት ማሰባሰብያ ዉይይት አድርጓል፡፡

ዉይይቱ ላይ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተውጣጡ ዳኞች እና ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ተሳትፈዉበታል፡፡ 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን በፍትህ ስርዓቱ የሚያልፉ ህፃናት ጥቅምና ደህንነታቸዉ ተጠብቆ እንዲያልፉ ምቹ የፍትህ ስርዓት በመዘርጋት ነገን የሚያልሙና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር እንዲህ አይነት መመሪያዎች ድርሻቸዉ ከፍ ያለ ከመሆኑም ባሻገር ፍርድ ቤቶች ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖራቸዉ በማድረግ ረገድ ሚናዉ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

መመሪያዉ በ2008 ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ያዘጋጀዉን መመሪያ፤በስራ ላይ ያለዉን የኦሮሚያ ክልል የህፃናት ቀለብ አወሳሰን ማንዋል፤የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎች እና የጥናት ግኝቶት በግብዓትነት ተጠቅሟል፡፡

መመሪያዉን ለማዘጋጀት የተደረጉ የዳሰሳ ጥናት መነሻ ሂደቶች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክብርት ወ/ሮ እትመት አሰፋ የቀረበ ሲሆን ረቂቅ የህፃናት ቀለብ አወሳሰን መመሪያ በጠበቃ አቶ ጌዲዬን ሲሳይ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የቀረበዉን የመመሪያ ፅሁፍ መነሻ በማድረግ በቀጣይ መካተት ስላለባቸዉ ተጨማሪ ግብዓቶች፣ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸዉ ቀለብ ከፋይ ላይ ዉሳኔ ለመወሰን የሚያስችሉ አቅጣጫዎች፣ መች ቀለብ መወሰን እንዳለበት፣ ቀለብ በገንዘብና በአይነት በሁለቱም አማራጮች መቅረብ የሚችልበት አግባብ፣ በማንኛዉም ሁኔታ ያለ ቀለብ ሰጪ ዝቅተኛ መነሻ እና ሬንጅ በተመለከተ፣ ቀለብ የሚጀመርበትና የሚቋረጥበት ወጥ ጊዜ ፣ ቀለብ ሰጪ የሌላቸዉ ህፃናት ድጋፉን የሚያገኙበት አማራጮች፣ በፅንስ ላይ ያለ ህፃን ቀለብ በተመለከተ፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸዉ ህፃናት የቀለብ አወሳሰን እና የህፃናት ቀለብ ጉዳይ የያዙ መዛግብት ቅድሚያ የሚሰጥበት ጉዳዬች ማካተት እንዳለበት እና በፅሁፉ ማብራሪያና ግልፅነት የሚያስፈልጋቸዉ ሃሳቦች ተብራርተዉ እንዲቀርቡ ሰፊ ዉይይት ተደርጓል፡፡

ዉይይቱን የመሩት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ ተክለሀይማኖት ዳኜ በዉይይቱ የቀረቡ ግብዓቶችን በመዉሰድ በቀጣይ ረቂቅ መመሪያዉ ተጠናከሮ እና ዳብሮ እንደሚቀርብ ገልፀዋል፡፡

Previous Article ዜና ሹመት
Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስራ ሃላፊዎች የፕሮጀክት አስተዳደር ስልጠና
Print
2295