በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕጎችና አዋጆች ሲወጡ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
/ Categories: News

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕጎችና አዋጆች ሲወጡ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አገራችን በርካታ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን የተቀበለች እና በርካታ የሕግ ድንጋጌዎች ያሏት በመሆኑ ሕጎቹን ትኩረት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማስተካከል፣ ወደፊት የሚወጡ ሕጎችንና አዋጆችን ደግሞ ይህን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ማየት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሕግ፣ ዲሞክራሲና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ አስገነዘቡ፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሕግ፣ ዲሞክራሲና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ለጤና እና ማህበራዊ ጉዳየች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ለሴቶች ካውከስ አባላት እንዲሁም ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና አመራሮች በሴቶችና ሕጻናት መብቶች ዙሪያ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ቢሾፍቱ በሚገኘው አዱላላ ሪዞርት እና ስፓ ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሒዷል፡፡

የተከበሩ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ በውይይት መድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት አዲስ የሚወጡ ሕጎች ለጥቃት የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ምን ያህል የጠብቃሉ የሚለውን ጉዳይ የም/ቤት አባላት ትኩረት የሚሰጡትን ያህል ሕግ ተርጓሚ የሆኑት ዳኞችም ለሕጉ አተረጓጎም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕጻናት ፍትሕ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ ተክለሐይማኖት ዳኜም በበኩላቸው ከፍተኛ ክብደት እና ቦታ በሚሰጠው በወንጀል ሥነስርዓት እና ማስረጃ ህግ ላይ ምክር ቤቱ ከፍርድ ቤቶች ጋር በቅርበት መስራቱ በተግባር በዳኞች የሚታዩ ክፍተቶችን በመፍታት እንዲሁም የተከራካሪዎችን እንዲሁም የህብረተሰቡን መብት በማስጠበቅ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው ሁለቱ የመንግስት አካላት በቅርበት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በሴቶችና ሕጻናት መብቶች እንዲሁም በወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ ገብተው በሚገኙ ሕጻናት ዙሪያ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት በዳኛ አሸነፈች አበበ፣ በዳኛ ልዑለስላሴ ሊበን እና በወ/ሮ ሴፋኒት መኮንን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በረቂቅ ደረጃ ባሉት የወንጀል ሥነሥርዓት እና የማስረጃ ሕጎች ላይ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ድንጋጌዎች ላይ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጋር የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በድብቅ የሚፈጸሙና ውስብስብ በመሆናቸው ልዩ የምርመራ ዘዴ ሊደነገግላቸው እንደሚገባ እንዲሁም የወንጀሉን አፈጻጸም ሚስጢራዊነት ታሳቢ ከማድረግ አንጻር አቃቤ ሕግ በበቂ ሁኔታ ተጠርጣሪው ወንጀል ስለመፈጸሙ በሚያስረዳበት ጊዜ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስላለመፈጸሙ ማስረጃ እንዲያቀርብ ሆኖ ሕጉ እንዲሻሻል አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

ከጽሑፍ አቅራቢዎቹና ከአስተያየት ሰጭዎቹ በጉዳዩ ላይ የተሰነዘሩ በርካታ ሀሳቦች በግብአትነት ሊውሉ እንደሚችሉ አስተያየት በተሰጠበት መድረክ የጾታዊ ጥቃት ጉዳይን የም/ቤት አባላት ክትትልና ግምገማ የሚያደርጉበት አሠራር ተግባራዊነትም ከግምት እንዲገባ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ብርሐነመስቀል ዋጋሪ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር በሴቶችና ሕጻናት ጥቃት ላይ ለውጥ ለማምጣት የፌደራል ፍ/ቤቶች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በዘርፉ ውጤት ለማምጣት የሁሉም ሕብረተሰብ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራትጅክ ዕቅድ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ አንድ ግብ የተቀመጠ መሆኑ ተገለጸ
Next Article "ፍርድ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል"-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
Print
532