Monday, April 14, 2025 / Categories: News በስዊድን የልምድ ልውውጥ ያደረጉ የፌደራል ዳኞች ከሶስቱም ፍርድ ቤት ለተውጣጡ ዳኞች ልምዳቸውን አካፈሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከ UNODC (United Nations I Office on Drugs and Crime) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ በስዊድን አገር የልምድ ልውውጥ አድርገው የተመለሱ የፌደራል ዳኞች ከሶስቱም ፍርድ ቤት ለተውጣጡ ዳኞች ልምዳቸውን አካፍለዋል። በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍረድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በቅርቡ 23 የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች ወደ ስዊድን አገር ፍርድ ቤቶች ጉብኝት በማድረግ ልምድ መቅሰማቸው አውሰተው መሰል የልምድ ልውውጥ መርሃግብሮች ዳኞች ተግባር ተኮር የሆነ እውቀት እና ልምድ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ በዘርፉ ከሚደረጉ ሌሎች የማሻሻያ ስራዎች ጋር ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡ በUNODC (United Nations Office on Drugs and Crime) የወንጀል መከላከልና የወንጀል ፍትህ እና ጸረ ሙስና ኃላፊ የሆኑት ክብርት ሚስ ቻሪቲ ካግዊ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ከ UNODC (United Nations Office on Drugs and Crime)ጋር በትብብር ለመስራት እድሎችን በማመቻቸት ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በወንጀል ፍትህ ስርአቱ ጋር በተገናኘ በትብብር ለመስራት ከመቼውም ግዜ በበለጠ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመድረኩም የልምድ ልውውጡ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ክቡር ዳኛ ተፈሪ ገብሩ (ፒ.ኤች.ዲ) እንዲሁም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ክብርት ዳኛ ህልውና ነስሩ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪፎርም አድቫይዘር አቶ ምስጋና ደቢሳ የስዊድን መጀመሪያ ደረጃ፣ ይግባኝ እንዲሁም ሰበር ስርዓት እና ሌሎች ተሞክሮዎች ላይ ጽሆፎች አቅርበው ከክቡራን ዳኞች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ባስላለፉት መልዕክት ከእንዲህ ዓይነት የልምድ ልውውጥ ለውጥ ማምጣት የሚችሉና መልካም የተባሉትን በመውሰድ ሊተገበሩ የሚችሉ የአሰራር፣ የአደረጃጀት እና የዳኝነት ስርዓት መስራት በሚቻለው ልክ ከሀገሪቷ ስርዓት ጋር በተናበበ መልኩ ወደ ተግባር በመለወጥ ዳኞች ለሀገር ግንባታ፣ ሰላምና መረጋጋት ያላቸውን የማይተካ ሚና ባገናዘበ መልኩ አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ Previous Article የUNODC (United Office on Drugs and crime) የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስ አሺታ ሚታል ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጋር ውይይት አደረጉ Next Article የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ Print 993