በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በተዘጋጀ ረቂቅ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ
/ Categories: News

በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በተዘጋጀ ረቂቅ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ

ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በጋራ በመሆን በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባዘጋጁት ረቂቅ የጥናት ሰነድ ላይ በቀን 22/03/2017 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሸሪአ ፍ/ቤት ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ችግሮቹን ከመሰረታቸው በማጥናት እንደ ችግሮቹ አይነት፣ መጠንና አንደምታ መፍትሄ ለመስጠት በማሰብ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ከሸሪአ ፍ/ቤትና ከኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተውጣጡ አባላትን በኮሚቴነት በማደራጀት የጥናት ውጤቱ ሊቀርብ መቻሉን አንስተው ጥናቱ አሁናዊ ችግሮችን ብቻ ለመፍታት ብቻ ሳይሆን መጪውን ግዜም ማገልገል የሚያስችሉ ሀሳቦችን ያመነጨ በመሆኑ በዚህ ላይ ሀሳቦች ተንሸራሽረው ነባራዊ ሁኔታው በሚፈቅደውና ተቋማቱን ወደፊት ማሻገር የሚያስችል መግባባት ላይ ለመድረስ ከውይይቱ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አክለውም በጥናቱ የተለዩ ችግሮች አግባብነት፣ ብቁነት እንዲሁም ሽፋን ላይ የሚሰጡ ግብዓቶች ጥናቱን ከማዳበር ባለፈ በቀጣይ የሚዘጋጀው ረቂቅ ህግን ጥራት ከፍ በማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ማገዝ በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት የተከበሩ ዶ/ር ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ለሚያደርገው ቀና ትብብርና ለተጀመረው ትልቅ እድል አመስግነው ህገመንግስቱን፣ የሀገሪቱን አንድነት፣ ፍቅር፣ ክብር በጠበቀ መልኩ የሙስሊም ማህበረሰቡ በህግና በሸሪአ መሰረት የሚገለገልበት ሸሪዓ ፍ/ቤትን ለማደራጀት አሰራሮችና ህጎች የሚሻሻሉና የሚለወጡ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ አባላትም በጥልቀትና በተፈተሸ መልኩ ለውጤት ላበቁት ጥናት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር ሸህ ሙባረክ ሸህ መሐመድ አወል ባደረጉት ንግግር ለብዙ አመታት ሸሪአ ፍ/ቤት ላይ ችግሮች የነበሩ መሆኑን፣ ችግሮቹንም ለመቅረፍ ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ የነበረ መሆኑን፣ በብዙ ምክንያቶች ሳይሳካ የቀረ መሆኑን፣ አሁን ግን በዚህ መልኩ ጥናት ተደርጎ መቅረቡ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሃላፊ ክቡር ኡስታዝ አቡበክር በበኩላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በሸሪዓ ፍ/ቤት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል የነበረው ዝግጁነትና ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነና ጉዳዩ መሬት እንዲወርድና ሸሪዓ ፍ/ቤት በሚመጥነው ቁመና ላይ እንዲገኝ በተደረገው ሂደት ላይ ሃላፊነቱን በመውሰድ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ጥናቱን በማጥናትና ሰፊ ውይይት በማድረግ ስራውን ያቀረቡትን ከሶስቱም ተቋማት የተውጣጡ የኮሚቴ አባላትንም አመስግነዋል፡፡ እንደ ሙስሊም ማህበሰረሰብ እየተሰሩ ካሉ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ከሚይዙት መካከል አንዱ የሸሪአ ፍ/ቤት ጉዳይ በመሆኑ ሶስቱም ተቋማት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ወደ ጥሩ ጅማሮ የተመጣ መሆኑንና ውጤታማ በመሆን ለውጡ ታይቶ በአጭር ግዜ ውስጥ ተቋሙ በሚገባው ቁመና እንደሚደራጅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ሰነዱ ላይ የግብዓት ማሰባሰብና የማዳበር ስራዎችን በመስራት ረቂቅ አዋጅ ወደማዘጋጀት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

Previous Article የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተገልጋዮች ለፍ/ቤት የሚቀርቡ መዛግብትን ባሉበት አካባቢ ሆነው ማስከፈት የሚችሉበት (e-filing) ሶፍትዌር እና የዳኞች መዝገብ መከታተያ ( judge’s Dashboard) ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ
Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአምስት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይትና ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል
Print
983