Anonym / Tuesday, July 13, 2021 / Categories: News በቅርቡ የፀደቁ የፍርድ ቤቱን አዋጆች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት እየተፋጠነ ነው ማሻሻያ ተደርጎባቸው በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፀደቁትን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 እና የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት እየተፋጠነ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ረቂቅ መመሪያ ላይ ግብአት ለማሰባሰብ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቤስት ዌስተርን ሆቴል የተካሔደውን የውይይት መድረክ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት አዋጆቹን ወደተግባር ለማስገባት ቁጥራቸው 21 የሚደርስ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ ዝግጅታቸው እየተጠናቀቀ ከሚገኘው 12 ያህል ደንቦችና መመሪያዎች መካከል በቅርቡ ተሻሽሎ በጸደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 የሕግ ዕውቅና ያገኘው ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መሆኑን የገለጹት ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ፣ ይህንኑ ተፈጻሚ ለማድረግ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዝርዝር መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል አዋጁ በደነገገው መሠረት የመመሪያው ዝግጅት በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮች በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት የሚያልፉበትንና ዕልባት የሚያገኙበትን ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ ዝርዝር ድንጋጌ የያዘው ይህ ረቂቅ መመሪያ በስምንት ምዕራፎች እና በ49 አንቀጾች የተከፋፈለ ሲሆን በመድረኩ ላይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤት አስማሚነት አስተባባሪ በሆኑት በአቶ ዮናስ ግርማ ቀርቦ በተሳታፊዎቹ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና ከአዲስ ከበባ ከተማ ፍርድ ቤት የተወከሉ ዳኞች፣ ረዳት ዳኞች፣ ጠበቆች እና የሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም የፍርድ ቤት አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ከመድረኩ ረቂቅ መመሪያውን ለማዳበር የሚያስችሉ ጠቃሚ ግብአቶች ቀርበዋል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ሲጸድቅ ተፈጻሚ የሚሆነው በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የፌደራል ጉዳይን የክልል ፍርድ ቤቶች በውክልና ሥልጣናቸው በሚያዩበት ጊዜ በሚቀርቡ የፍታብሔር ጉዳዮች በባለጉዳዮቹ ነጻ ፈቃድ ላይ በተመሠረተ ሁኔታ እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከሚቀርቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮች መካከል በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት የሚያልፉት የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ፣ የቤተሰብ ጉዳይ፣ የውርስ ጉዳይ እንዲሁም ከንግድ እና ከግንባታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደሚሆኑም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤት መር አስማሚነት አገልግሎት በሙከራ ደረጃ በተወሰኑ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ችሎቶች እየተተገበረ የሚገኝ ሰሆን ረቂቅ መመሪያው ሲጸድቅ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስፈልጉ ቅድመ-ዝግጅቶችን በማሟላት ለባለጉዳዮች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ይሆናል፡፡ የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጆች በቅርቡ መጽደቃቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለጀመሩት የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው የተገለጸ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ትግበራ ማስጀመሪያ ውይይት ተካሄደ Next Article በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ መዋቅር ላይ ምክክር ተካሄደ Print 2958 Gallery