በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ላይ ለፌደራልና ለክልል የፍትሕ ተቋማት ተሳታፊዎች ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ
/ Categories: News

በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ላይ ለፌደራልና ለክልል የፍትሕ ተቋማት ተሳታፊዎች ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ

በአገራችን ፍርድ ቤቶች የቅጣት ውሳኔዎችን ወጥነት እና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መኖር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንኑ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 88(4) በተሰጠው መሠረት ፍርድ ቤቱ በቅርቡ አሻሽሎ ባወጣው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ላይ ለፌደራልና ለክልል የፍትሕ ተቋማት ተሳታፊዎች ከሐምሌ 10-12 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡

የአሠልጣኞች ሥልጠናው የተሰጠው የቅጣት አወሳሰን መመሪያው ከሚመለከታቸው 34 ተቋማት ለተወከሉ የፌደራል እና የክልል ፍ/ቤቶች ዳኞች እና ሌሎች የፍትሕ ተቋማት ተሳታፊዎች ሲሆን በሥልጠናው ላይ ሽፋን የተሰጣቸው ርዕሰ-ጉዳዮችም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ዝግጅት እና ዋና ዋና ሐሳቦች፣ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ታሳቢዎች፣ የወታደራዊ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን፣ በግብረ ሥጋ ነጻነት እና ንፅሕና ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን እና መርዛማ ወይም የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶች ማምረት፣ መጠቀም፤ በሰው ሕይወት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በሰው አካል ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የተሻሻለ የቅጣት አወሳሰን ላይ ነው፡፡

በተጨማሪም ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የወጣውን በመተላለፍ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ በመተላለፍ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን እንዲሁም የቅጣት አሰላል እና ስለቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ምክንያቶች አያያዝ እና በሙስና ወንጀሎች እና በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ቅጣት አወሳሰን ላይ የተሻሻለውን መመሪያ መሠረት በማድረግ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

የአሰልጣኞች ሥልጠናው የተሰጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሆኑት እና በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ዝግጅት ላይ ተሳትፎ ባደረጉት በዳኛ ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)፣ በዳኛ ተሾመ ሽፈራው እና በአውሮፓ ሕብረት በሚደገፈው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከፍተኛ አማካሪ በሆኑት በአቶ ብዙኃ ሙሉጌታ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ በሆኑት በዳኛ ፈይሳ በዳዳ እንዲሁም ቀደም ሲል የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት በነበሩት እና የአርቃቂ ቡድኑ ሰብሳቢ በሆኑት በክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል ነው፡፡

መመሪያውን በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲቻልም በዚህ የአሠልጣኞች ሥልጠና የተሳተፉ ሠልጣኞች ከመድረኩ ያገኙትን ግንዛቤ በራሳቸው ሥራ ላይ እንዲያውሉት የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች የሥራ አጋሮቻቸው እንዲያካፍሉ ለማስቻል ይህ የአሠልጣኞች ሥልጠና መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያም የአርቃቂ ቡድኑ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን ያዘጋጀውን ልምድ ያላቸው ዳኞች ያሉበትን ኮሚቴ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤትን አመስግነው የወንጀል ሕጉን ግብ ለማሳካት ቅጣት አንድ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው፣ የተከለሰው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ትክክለኛነት እና ወጥነትን በሚያረጋግጥ አግባብ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ መመሪያው ከወረዳ ጀምሮ እስከጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሉ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመው ሕዝቡ ከየትኛውም የወንጀል ስጋት ነጻ እንዲሆንና ወንጀል የፈጸሙም ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ፣ ነጻ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን ደግሞ ነጻ እንደሆኑ በሚያሳይ አግባብ ሁሉም ኃላፊነቱን ከተወጣ የፍትሕ ሥርዓቱን በሕዝብ የታመነ እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ማድረግ ስለሚቻል ይህ እውን እንዲሆን ሁሉም የፍትሕ አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስምረውበታል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 1/2002) በ2002 ዓ.ም ያወጣ ሲሆን በ2006 ዓ.ም ደግሞ የተሻሻለውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 2/2006) አውጥቶ ላለፉት 11 ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን የቆዬ ሲሆን ይህ መመሪያ ያሉበትን ክፍተቶች በጥናት በመለየት እና ከመመሪያው አፈጻጸም ጋር የሚገናኙ ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ መመሪያ ቁጥር 3/2017 ወጥቷል፡፡

Previous Article የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት ተመረቀ
Next Article የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእውቅና ሽልማት አበረከተ
Print
1094